አከራዮች፤ የተከራዮቻቸውን ማንነት በሳምንት ውስጥ ለፖሊስ እንዲያስመዝግቡ ታዘዘ

ማንኛውም ቤት አከራይ የተከራይን ማንነት የሚገልጽ ሙሉ መረጃ፤ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ እንዲያስመዘገብ የአስቸኳይ ጊዜ ዕዝ ትዕዛዝ ሰጠ። በትዕዛዙ መሰረት ምዝገባውን የማያከናውኑ አካላት ላይ አስፈላጊው ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ አስተላልፏል። 

ዕዙ ዛሬ ረቡዕ ህዳር 1 ምሽት ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ትዕዛዙ የተላለፈው “የጸጥታ ኃይሎች ለሕዝቡ ደኅንነት ሥጋት የሚሆኑትን ለመመንጠር ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲያግዝ” ነው። “የጸጥታ ኃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌዎችን በማስፈጸም ባለፉት ቀናት አኩሪ ውጤቶችን አስመዝግቧል” ያለው ዕዙ፤ ይህንን ተከትሎ “ሕገ ወጦች” ያላቸው አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን አስታውቋል።

“ይህ ያስደነገጠው  ጠላት የጸጥታ አካላትን መልካም ስም ለማጥፋት፣ ለማሸማቀቅና ሥራቸውን በሙሉ አቅም እንዳይሠሩ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ  ይገኛል” ሲልም ዕዙ በዛሬው መግለጫው አመልክቷል። ከዚህ ጎን ለጎን “በአጋጣሚው ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የጸጥታ አካላት መኖራቸውን” አረጋግጬያለሁ ብሏል ዕዙ። “በእነዚህ አካላት ላይ፤ በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ተሰጥቷል” ሲልም በመግለጫው ጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

The post አከራዮች፤ የተከራዮቻቸውን ማንነት በሳምንት ውስጥ ለፖሊስ እንዲያስመዝግቡ ታዘዘ appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply