አየር መንገድ ውስጥ እየተፈጠረ ስላለው የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ስነምግባር ጉዳይ ምን ተባለ?ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ተለያዩ ዓለም ዐ…

አየር መንገድ ውስጥ እየተፈጠረ ስላለው የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ስነምግባር ጉዳይ ምን ተባለ?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ተለያዩ ዓለም ዐቀፍ መዳረሻዎች የሚጓዙ መንገደኞች በቦታው ባሉ የኢሚግሬሽን ሠራተኞች ምክንያት ከጉዟቸው እየተስተጓጎሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ቅሬታቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡

አየር መንገድ ውስጥ የሚገኙ የኢምግሬሽን ሰራተኞች በሚፈጥሩት ጫና ምክንያት ተጓዦች እየተማረሩ ስለመሆናቸው ይነገራል፡፡

ትልቁ የአገሪቱ የደህንነት ተቋም በሙስናና ብልሹ አሰራር ውስጥ በመዘፈቁ ዜጎች ብቃት ያለው አገልግሎት አጥተው በገዛ አገራቸው ለእንግልትና ለመከራ መዳረጋቸው እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰራተኞቹ ከህግ አግባብ ውጪ በሚፈጥሩት ወከባ ምክንያት ተጓዦች በረራዎች እንዲያመልጧቸው ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ።

በተለይ ደግሞ በተደጋጋሚ ለንግድ ወደ ውጭ አገራት የሚመላለሱት ተገልጋዮች ጉዳዩ ስር የሰደደ ነው ይላሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ችግሮች እየተባባሱ መምጣታቸው ሁኔታውን የከፋ እንዲሆን አደረገው እንጂ ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ይህን ዓይነት ችግር ይስተዋል ነበር” ሲሉ ቅሬታቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች ያጋሩ ተገልጋዮች ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከበረራ ሰዓት አስቀድሞ የጉዞ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላትና ሻንጣዎችን ጭኖ መመለስ ይቻል የነበረው አሰራር መከልከሉ  አሁን ላይ እንደማይሰራ የሚናገሩት ተገልጋዮች በተለይ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች የሚፈጥሩት ወከባ እና ማንገላታት አማሮናል ሲሉ ነው ሚናገሩት፡፡

የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በኢሚግሬሽን ሰራተኞች በኩል እየደረሰባቸው ያለውን እንግልት ያጋሩት ተገልጋዮች መ/ቤቱ ከጊዜ ወደ ግዜ አገልግሎት አሰጣጡ እያሽቆለቆለ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በተለይ ወደ መካከለኝ ምስራቅ አገራት ለስራ የሚጓዙ በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ መጉላላት፣ እንግልት እንደደረሰባቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምላሽ

የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ዳሬክተር የሆኑት ማስተዋል ገዳ ከተገልጋዮች የተሳው ቅሬታ እና ጥቆማ እንደደረሳቸው ተናግረው ከመስራቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ቦሌ አየር ማረፍያ ከሚገኝው የስራ ተቆጣጣሪ ጋር በመሆን በጉዳዩ ላይ ምክክር እየተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

አንዳንዴ ካለመናበብ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች መኖራቸውን የተናገሩት ዳሬክተሯ ማንኛውም ዜጋ የሚጠበቅበትን መረጃ ካሟላ አገልግሎቱን ማግኝት መብቱ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም ሰራተኞች ተመሳሳይ ስነምግባር ላይኖራቸው ይችላል ያሉት የኮሚኒኬሽን ዳሬክተሯ ስነምግባር የጎደላቸው ሰራተኞችን ተቋሙ የሚታገስበት ምንም ምክንያት አይኖረውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዜጎች በአየር መንገድ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ የኢሚግሬሽን ሰራተኞች ያልተገባ እንግልት እንደሚደርስባቸውና ገንዘብም እየተጠየቁ ያሉ መኖራቸው ተጠቅሶ ያውቁት እንደሆን የተጠየቁት የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሯ እየተጣራ የማያዳግም እርምጃ የመውሰድ ሥራ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

ፓስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የገንዘብ መቀበያ ሰነድ የሚሸጡ ፣ የኢሚግሬሽንን ሰነዶች በማስመሰል እና ቅድሚያ ታገኛላችሁ በሚል ማጭበርበር መኖሩን ፣ የተቋሙን የውስጥ ሰነዶችን ወደ ውጪ ማስወጣት ኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት የለያቸው ችግሮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

Source: Link to the Post

Leave a Reply