“አይቆረጠም የድንጋይ ቆሎ ፣ አይወረወር የእሳት አለሎ ፣ ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ”

“አይቆረጠም የድንጋይ ቆሎ

አይወረወር የእሳት አለሎ

ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ”

ባሕር ዳር ፡ የካቲት 14/2013 ዓ.ም (አብመድ

ምድሩ ያስፈራል፣ ጎዳናው ያደናግራል፣ ጋራው ሸንተረሩ ሁሉ ጀግና ጀግና ይላል። ከላሞቹ ወተት፣ ከበሬዎቹ እሸት፣ ከጠመንጃው ጥይት፣ ከልጆቹ ጀግንነት፣ ከትውልዱ ኢትዮጵያዊነት አይነጥፍም፣ ኢትዮጵያ በቤቱ፣ በሕይወቱ፣ በደምና ባጥንቱ፣ በአንደበቱ ተዋህዳ አትጠፋም። ወዳጁን ያጎርሳል፣ በመልካም እጁ እንደ እናት ይዳስሳል፣ አውልቆ ያለብሳል፣ ወንዝ አሻግሮ ከመልካም ነገር ያደርሳል፣ ጠላቱን በጦር በሳንጃ እጅ ይነሳል፣ ተመልከት ብሎ ጅማት ይበጥሳል። ኢትዮጵያ ሀገሩን የነካ ሁሉ ወዮለት እጣው ሞት ነው።

የዚያኔው ሰሜን በጌምድር ግዛት ኢትዮጵያ ተነካች በተባለ ቁጥር ነፍጡን እያነሳ በዱር በገደሉ እየወረደ ጠላቱን ሲመልስ ኖሯል። ዛሬም ይመልሳል።

“እኒህ ጎንደሮች አርማጭሆች

እኒህ ጠገዴ ወልቃይቶች

በደም ለውጦ ጥይት አምራች

እስከ ትክሻው ብሬን አንጋች

ሀምሳ ስልሳ ጫን እህል አምራች” ወደ ሚባልላቸው ተጉዤ ነበር። ፈጣሪ ያን ሥፍራ ለጦርነት፣ ለምርት፣ ሰዎቹን ደግሞ ለጀግንነት አዘጋጅቷቸዋል። በዚያ ምድር ብቻን መብላትና መጠታት፣ አሳብ አልቦ መተኛት፣ ትጥቅ ፈትቶ መዘናጋት አይታወቅም። ሁልጊዜም ዝግጁ ነው ሕዝቡ። ሰላም ሲሆን ማረስ፣ ችግር ሲመጣ መተኮስ ልማዱ ነው።

“ድው ድው የሚለው ክላሽ ሳይመጣ

ድርን የሚለው ብሬን ሳይመጣ

ጋሻ መክቶ ጦር እየቀጣ

እየጋጋረ ኮሾና ቂጣ

ቆሎ ቆርጥሞ ውኃ እየጠጣ

ሀገሩ ኢትዮጵያን ነፃ ሚያወጣ” ይባልላቸዋል።

በዚያ በኩል ያልሞከረ፣ በጀግኖች ክንድ ያልተሰበረ፣ በጦር ተወግቶ ያልተባረረ የለም። የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላቶች መቅናቸው

የሚፈሰው፣ ጉልበታቸው የሚኮስሰው፣ ደማቸው የሚፈሰው፣ አጥንታቸው የሚከሰከሰው፣ ሬሳቸውን ዳዋ የሚያለብሰው በዚያ ምድግ ሲደርሱ ነው። አያሌ የጠላት ክንዶች ተነሱ፣ ሁሉም እጅ እየነሱ፣ በጀግኖች ክንድ እየተመለሱ ወደ መጡበት ተመለሱ። ለጦርነትና ለጀግንነት የታደለው የሀገሬው ሰው አልቀመስ አለ። ሀገር ተከበረች፣ ኢትዮጵያ ታፈረች፣ በጀግና ልጆቿ ስም በአሸናፊነት ናኘች።

ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከረችው ጣልያን ድል ሆና ተመለሰች። ክርስቶስ ከተወለደ ወዲህም ዳግም መጣች ተሸንፋ ተመለሰች፣ ዘመን ጠብቃ ሽንፈቷን ረስታ፣ ኃይሏን አደራጅታ በዓድዋ ዘለቀች ዳግም ተሸነፈች፣ ኃያልነቷን አሳንሳ ኢትዮጵያን አንግሳ ተመለሰች። የሮምን የጦር መሬዎች የኢትዮጵያውያን ጎራዴ በላቸው፣ ሳንጃው ጠጣቸው፣ የሽንፈት ታሪካቸውን አጠናክረው ሌላ የሽንፈት ታሪክ ፅፈው ተመለሱ።

ሮም አንገቷን ደፋች፣ በዓለም ፊት ተዋርዳለችና ኮሰመነች፣ ኢትዮጵያ በኩራት ከፍ አለች፣ ከተራራው አናት አምሳለ ቀስተ ደመና የሆነውን ባንዲራ እያውለበለበች ድምጿን ከፍ አድርጋ ሁልጊዜም አሸናፊዋ እኔ ነኝ አለች። ኃያላኑ ፈሯት፣ አከበሯት፣ ወዳጅ ትሆናቸው ዘንድ ተመኟት፣ ፍቅርሽን እንሻለን ሲሉ ለመኗት። ከልቡ ለሚያፈቅር ፍቅር፣ ከልቡ ለሚጠላ ጦር እንደ አመጣጡ የምትሰጠው ኢትዮጵያ አትንኩኝ እንጂ ፍቅርን ከእኔ በላይ የሚያውቀው የለም አለች።

ዘመን አለፈ። ሌላ ዘመን መጣ። የሮም ነገሥታት፣ መኳንንት እና መሳፍንት አንገታቸውን ቀና ያደርጉ ዘንድ ተመኙ። ሌላ እድል ሞከሩ። ግርማዊ ጃንሆይ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ አሰፈሪውን ዙፋን ተቀምጠውበታል። እሳቸውና ሕዝባቸው ፍቅር ሲሹ በሮም ለአርባ ዓመታት የተደገሰ የጦር ድግስ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። የአባቶቻቸው ልጆች ኢትዮጵያውያን ከጠላቶቻቸው ጋር ይፋለሙ ጀመር። እንደ ዓድዋው በአንድ ጀንበር ድል አልተገኘም። የጠላት ጦር ኢትዮጵያን እየወረረ ሄደ። የአርበኝነት ሥራ ተጀመረ።

በዚያ ዘመን በአርበኝነት የጣልያንን ሠራዊት ቁም ስቅል ካሳዩት ኢትዮጵያውያን መካከል የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት አርበኞች በጉልህ ይነሳሉ። እግሬ ጠገዴን ሲረግጥ ያን ዘመን አስታወሰ። በዚያ ዘመን በአርበኝነት ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱት መካከል ቢትወደድ አዳነ መኮንን አሰብን። በሰሜን በጌምድር እልፍ አርበኛ፣ እልፍ ጦረኛ፣ እልፍ ነፃነት ፈላጊ፣ እልፍ ሳይሰለች ተዋጊ ነበር። ከእነዚያ ጀግኖች መካከል ቢትወደድ አዳነ መኮንን ላስታውሳቸው ፈለኩ።

“ማረሻው ምንሽር መጎልጎያው ጓንዴ

የአባ ደፋር ሀገር ወልቃይት ጠገዴ” የተባለላቸው አባ ደፋር አዳነ በየጦር ግንባር እየዘመቱ፣ ጠላትን ድል እየመቱ፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖር አድርገዋል። በጠገዴ አዴት የተወለዱት ቢትወደድ አዳነ መኮንን ገና በልጅነታቸው ነበር ማረስና መተኮስ የተለማመዱት። ለአደን ሲወጡ ያለ ግዳይ አይመለሱም ነበር። ጦር አዋቂነታቸው ጉድ ያሰኝ ጀመር። ቀልብ ሳቡ ። ስማቸው መግነን ጀመረ። ቢትወደድ አዳነ በዚያ ዘመን ሰሜን በጌምድርን ሲያስተዳድሩት የነበሩት ራስ ጉግሳ ወሌ ሠራዊት ጋር ተቀላቅለው ኢትዮጵያን ማገልገል ጀመሩ። የጦር ስልት ያደጉበት ነበርና በጦር ስልታቸውና ድፍረታቸው የተገረሙት ራስ ጉግሳ ወሌ የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ሰጧቸው።

አባ ደፋር ቢትወደድ አዳነ ራስ ጉግሳ ካለፉ በኋላም በሰሜን በጌምድር የወልቃት ጠገዴን፣ የአርማጭሆንና የሰቲት ሁመራን ድንበር እንዲጠብቁ ተመረጡ። ከጀግኖች አርበኞች ጋር በመሆንም በዚያ በር ጠላት እንዳይላወስ ያደርጉ ነበር። የጣልያን ሠራዊትን ካርበደበዱ አርበኞች መካከል የጠገዴውን ጦር እየመሩ አያሌ ጀብዱዎችን መፈፀማቸውን የቢትወደድ አዳነ የልጅ ልጅና ታሪክ አዋቂ ሹምዬ ወልደ ሥላሴ ነግረውኛል። የእናታቸው አባት ቢትወደድ አዳነ በዚያ ዘመን ከነበሩ አርበኞች ጋር በመሆን ጠላት በወልቃይት ጠገዴ፣ በአርማጭሆ፣ በጃንወራ፣ በቆላ ወገራ፣ በደባትና በሌሎችም አካባቢዎች ረግቶ እንዳይቀመጥ በእሳት ይቆሉት እንደነበርም ነግረውኛል።

የጣልያን ሠራዊት እየገፋ ሀገር ሲቆጣጠር እነ ቢትወደድ አዳነ በአዴት የአርበኝነት ሥራ ጀመሩ። በዚህ ጊዜ የጣልያን ሠራዊት ማይ ገና የተባለውን አካባቢ ዙሪያ ገባ ይዞ ነበር። እነ ቢትወደድ ደግሞ አካባቢውን ከጠላት ለማላቀቅ ተዘጋጅተዋል። የጠላትን ሠራዊት ለማሸነፍ ይረዳ ዘንድ ውኃውን ቀድሞ መያዝ አንደኛው እቅድ ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ ዳኛቸው የተባለ አርበኛ

“አዴት ማይ ገና ላይ ካልተሠራ ቤቴ

ወንድም አልወለደች መካን ናት እናቴ” ሲል ጃሎ አለ። ጦሩ ተነሳ። ምድር ታመሰች። እነ ነብሮ ገቡ። የጠላት ጦር መድረሻ አጣ። አዴትንም ከጣልያን ሠራዊት ጋር ተዋድቀው አስለቀቁ። በአዴት ጦርነት በጀግንነታቸው የተገረመው የጣልያን የጦር መሪ “የሸፈቱት ሰዎች አምስት ናቸው ብላችሁኝ ነበር፣ እኔ ግን እንደ ምመለከታቸው መሬቱም ጭምር ሸፍቷል። ጥይት የሚመጣው ከመሬት ውስጥ ጭምር ነው” ማለቱን ገሪማ ታፈረ ፅፈዋል።

በዚያ የተገኘው ድል እየሰፋ ሄደ። ወደ ደጋው ጠገዴ አመሩ። ቀኝ አዝማች የነበሩት አዳነ በሕዝብ ይሁንታ ማክሰኞ ገበያ አጣጥ በተባለ ሥፍራ ሕዝቡ “ማዕረግ ኖሮዎት ለእኛም ማዕረግ እንዲሰጡን ደጅ አዝማች ብለን ሹመነወታል” ብሎ መሾሙንም ሹምዬ ነግረውኛል። እሳቸውም ለተከታዮቻቸው ማዕረግ ሠጡ። በሕዝብ የደጅ አዝማችነት ማዕረግ የተሠጣቸውና እሳቸውም የሠጡት ማዕረግ ንጉሡ ኃይለ ሥላሴ ሲመለሱ በደስታ አፅድቀውላቸዋል።

ጠገዴ ነፃ ወጣች። ወደሌሎች አካባቢዎች የአርበኝነቱ ሥራ ቀጠለ። የጃኖራ ቆላ ወገራ አርበኞች በደጅ አዝማች ሐጎስ ተሰማ፣ የአርማጭሆ አርበኞች በደጅ አዝማች ብሬ ዘገዬ፣ የጠገዴ አርበኞች በደጅ አዝማች አዳነ መኮንን፣ የጠለሎ አርበኞች በደጅ አዝማች ደስታ ማሩ፣ የደብረ ሐርያና የቀብትያ በፊታውራሪ መስፍን ረዳ፣ የአውራ አርበኞች በደጅ አዝማች አያናዬ ቸኮል እየተመራ ወልቃይትን ነፃ ለማውጣት ዘመተ።

የጣሊያን ሠራዊትም አድ ኮኮብ ላይ ሠፍሮ ነበር። አርበኛው ደግሞ ከአድ ኮኮብ በሥተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው የማይ ለሞን ተራራን ተጠግቶ ሠፈረ። እኒያ ጀግና አርበኞች ጠላትን እንዴት መግጠም እንዳለባቸው እየተመካከሩ በሠፈራቸው ቆዩ። ተከዜን ተሻግሮ ሰሜን በጌ ምድርን የረገጠው የጠላት ጦር ሲርቅ በባሩድ እሳት ይለበለባል። ሲቀርብ በሳንጃ ይመሸለቃል። የሚሆነውን አጥቷል።

አርበኛው በማይ ለሞን ተራራ እንደሠፈረ የደጅ አዝማች አዳነ መኮንን ጦረኛ የነበረ ሥጦት መኮንን የተባለ ጀግና ጦርነት ለመግጠም ቸኩሎ ነበርና በቢትወደድ አደነ ድንኳን አጠገብ ሆኖ እንዲህ ሢል ጃሎ አለ።

“ቂርቆስ ማይ ለመሞ የሁለት ፈሪ ሀገር

ወይ እነርሱ አይመጡ ወይ እኛ አንሻገር” እስኪ ድገመው አለ አርበኛው። ደገመው። ጦሩ ፎክሮ ተነሳ።

በግራ በኩል የአርማጭሆ አርበኛ በብሬ ዘገዬ እየተማራ፣ በቀኝ በኩል የጠለሎ፣ የቀብትያ፣ የደብረ ሐርያ፣ የአቀወርቅ፣ የአውራ አርበኛ በፊታውራሪ መስፍን ረዳና በደጅ አዝማች ደሥታ ማሩ እየተመራ፣ የጠገዴ አርበኛ በመሀል በደጅ አዝማች አዳነ መኮንን እየተመራ ውጊያ ገጠመ። በአዳነ መኮንን የሚመራው ጦር አስቀድሞ ከጠላት ሠፈር ደረሠ። የጠላትን ጦር እስከነ ባሩዱ ያቅመው ጀመር። ጠላት ማምለጫ አጣ። በቀኝ በግራ የገባው አርበኛ መፈናፈኛ አሳጠው። የጠነከረ ሮጦ አመለጠ። ያልቻለ እጅ ሰጠ። የፈረደበት እየተነደፈ ሞተ።

ገሪማ ታፈረ በጎንደሬ በጋሻው መፃሕፋቸው “በዚህ እልቂት የጠላት ወታደር ሬሳ ከአንድ አንድ ላይ ተከምሮ የኑግ ነዶ መስሎ ይታይ ነበር” ብለዋል። አርበኝነቱ ቀጠለ። ወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራን ነፃ አወጡ። ለዚያ አካባቢ ገዥ ሾመው።

ጣልያን ወዳለበት ሌላኛው የሰሜን በጌምድር አውራጃ ወደ ደባት አቀኑ። ድል በድል እየሆኑ ገሰገሱ። ጣልያን ተጨነቀ። ሠራዊቱ በጦር በጎራዴ አለቀ። በሰሜን በጌምድር አውራጃ ጠላት እየተለቀመ ወጥቶ ጎንደር ከተማ ላይ ሲቀር በአራቱም አቅጣጫ የሰሜን በጌምድር አርበኞች እየተመሙ መፈናፈኛ ሲያሳጡ ቢትወድድ አዳነ አንደኛው ነበሩ። ጎንደርም ተለቀቀች።

ቢትወደድ አዳነ በሱዳን ጠረፍ የኢትዮጵያን ድንበር ጠላት እንዳይረግጥ አያሌ ጀብዱዎችን እየፈፀሙ የተከላከሉ አርበኛም ነበሩ። ቢትወደድ አዳነ ወደጦር ሜዳ ከሄዱ መመለስ አይቻልም ነበርና

“አዳነ መጣ ጥርሱን አግጥጦ

ኧረ መጠጊያ ትንሽ ቁጥቋጦ” ይባልላቸው ነበር።

ጣልያንን በሚያርበደብዱበት ዘመን በማረኩት መትረጌስ የጣልያንን ተዋጊ አውሮፕላን ተመልከት ብለው እንደጣሉትም ይነገርላቸዋል ቢትወደድ አዳነ።

“አይቆረጠም የድንጋይ ቆሎ

አይወረወር የእሳት አለሎ

ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ” ተብሎላቸዋል።

እኒህ ጀግና ሰው የሰሜን በጌምድር የጦር አበጋዝ፣ የወገራ አውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው መሥራታቸውንም የልጅ ልጃቸው ሹምዬ ነግረውኛል።

በዘመናቸው ሀገር እንዳትደፈር ሲሉ ከተዋጉባቸው አያሌ የጦር አውድማዎች በተጨማሪ የሑመራ የሰሊጥ ምርት እንዲስፋፋ፣ የጎንደር ሑመራ መንገድ እንዲሠራና ሌሎች የልማት ሥራዎችን እንደከወኑም ይነገርላቸዋል።

የንጉሡ ዘመን ተጠናቆ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በአርማጭሆ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በሰቲት ሑመራ፣ በቆላ ወገራ፣ በአወጅሬ ጅንወራና በሌሎች አካባቢዎች ደርግ ደፍሮ እንዳይገባ ያደረጉ ሠው መሆናቸውንም የልጅ ልጃቸው ነግረውኛል።

“አዳነ አባ ደፋር ና ወንዱ ና ወንዱ

አላስሄደኝ አለ ሽፍታው በመንገዱ” እየተባለም ተገጥሞላቸዋል።

አባ ደፋር አዳነ ለሀገራቸው ነፃነት፣ ለኢትዮጵያዊነት፣ ለአይደፈሬነት ሲሉ ከጀግና አርበኞች ጋር ጦር መርተዋል። ገጥመው አሸንፈዋል። በዱር በገደል እየዋሉ እያደሩም ነፃ የሆነች ሀገር ሰጥተውናል። ያን አካባቢ እድል አግኝቶ ላየ ሁሉ ይገረማል። ልብ ይፈትናል። ጋራው ሸንተረሩ አጀብ ያሰኛል። ሁልጊዜ ጥንቁቅ የሆነው የሀገሬው ሠው ሲታይ አሞተ መራርነቱ ከፊቱ ላይ ያስታውቃል። ለሁሉም ዝግጁ የሆነ ምድር፣ ዝግጁ የሆነ ሕዝብ።

“ጦም እየዋሉ ጦም እያደሩ

በወይራ ቅጠል ቤት እየሠሩ

በድንጋይ ቂጣ እየጋገሩ

ሙሉ አምስት የተቸገሩ

ጀግና አርበኞች እኒህ ነበሩ”

ኢትዮጵያ የጀግኖች ምድር፣ ያልተመረመረች ሚስጥር፣ ያልተደፈረች ሀገር፣ የተገኘባት የሰው ዘር፣ ያልተቀደመች ምድር ናት። የቆመችው ሕዝቦቿ አብዝተው በሚለምኑት ፈጣሪ ጠባቂነት፣ በፀና ጀግንነት፣ በማይናወጥ አንድነት፣ በማይጠወልግ ኢትዮጵያዊነት ነው። ኢትዮጵያን የነካ ሁሉ እጣው መጥፋትና መሞት ነው። ክብር ለጀግኖቻችን። አንድነት ለሀገራችን።

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post “አይቆረጠም የድንጋይ ቆሎ ፣ አይወረወር የእሳት አለሎ ፣ ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ” first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.

Source: Link to the Post

Leave a Reply