አዲሱን የዓባይ ወንዝ ድልድይ ዋነኛ አካል የሆነውን ግሪደር በቀጣይ 3 ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለመግጠም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

የድልድዩ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀም 76 በመቶ ደርሷል

ሐሙስ መስከረም 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) በባህርዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘውን አዲሱ የዓባይ ወንዝ ድልድይ በቀጣይ 3 ወራት ውስጥ የድልድዩ ዋነኛ አካል የሆነው ግሪደር (Grider) ሙሉ ለሙሉ ለመግጠም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።

የድልድዩን ዋና ዋና ሥራዎች በእቅዱ መሰረት ለማከናወን አጠቃላይ የግንባታ ሂደቱ በመፍጠን ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀሙ 76 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

በእስካሁኑ የግንባታ እንቅስቃሴ ከ760 ሜትር (Girder) ርዝማኔ ውስጥ (በኹለት መስመር) 511 ሜትር የድልድይ (Grider) ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል።በግንባታው ፕሮጀክት ላይ በዋነኛነት የድልድይ ተሸካሚ ምሰሶዎች እንዲሁም፤ ከመሬት በታች የድልድዩ የቋሚ ተሸካሚ መሰረቶች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውም ተነግሯል።

ለድልድዩ የሚያስፈልጉ 8 ቋሚ ተሸካሚ መሶሶዎች ተከላ ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀና፤ ድልድዩን ወጥሮ ለመያዝ ከሚያግዙ 72 (Stay cables) አምሳው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የተቀሩትን በቅርብ ለመጨረስ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

በኢትዮጵያ መንግስት በተመደበ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ የተባለው ተቋራጭ ነው።

የማማከር እና ቁጥጥር ሥራውን ደግሞ ቦቴክ ቦስፈረስ ኮንሰልቲንግ ከስታዲያ ኢንጅነሪንግ ጋራ በጣምራ እየሰሩት ይገኛሉ።

አዲሱ የአባይ ወንዝ ድልድይ በባህር ዳር ከተማ ከሚገኘው ነባሩ የአባይ ወንዝ ድልድይ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው እየተገነባ የሚገኘው።

ይህ ዘመናዊ ድልድይ ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ከሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ጎን ለጎን ምቹ የሆነ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪም ባህር-ዳር ከተማ ተጨማሪ ውበት እንድትላበስ ይረዳታል።

ድልድዩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በግራና በቀኝ በአንድ ጊዜ 6 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይችላል፣ በተጨማሪም 5 ሜትር የእግረኛ መንገድ እንዲሁም የብስክሌት ተጠቃሚዎችን መስመር ባካተተ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝም አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply