አዲስ አበባ ለኗሪዎቿ ምቹ ለጎብኚዎቿም ሳቢና ማራኪ የምትሆነው ራሷን ሆና ስትገኝ ብቻ ነው- እናት ፓርቲእናት ፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ለዘመናት የተጣባን ኹሉንም አፍርሶ የመገንባ…

አዲስ አበባ ለኗሪዎቿ ምቹ ለጎብኚዎቿም ሳቢና ማራኪ የምትሆነው ራሷን ሆና ስትገኝ ብቻ ነው- እናት ፓርቲ

እናት ፓርቲ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ለዘመናት የተጣባን ኹሉንም አፍርሶ የመገንባት የተሳሳተ ጉዟችን በአስቸኳይ ሊታረም ይገባል ብሏል፡፡

በአገራችን ያለፉት ሃምሳ ዓመታት ጉዞ ከቀደመ ሥርዓት ጋር የተያያዘን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ አዲስ መሠረት መጣል ኹሉንም እንደ አዲስ የመገንባት የተሳሳተ አካሄድ ዛሬም ሊታረም አልቻለም ሲል ለጣብያችን ኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ይህ አካሄድ ከመንግሥትና የመንግሥታዊ ሥርዓት ግንባታ አልፎ ዛሬ ወደ ከተማና የከተማ ቅርስ በመዛመት በአዲስ አበባ እየተከናወነ በሚገኘው የነባር መንደሮችና ሕንጻዎች ፈረሳ የከተማችንን ታሪክ እያጠፋ ነውም ብሏል።

ፒያሳን ጨምሮ በሌሎች ሥፍራዎችም ነባር ሕንጻዎችን ወደ ፍርስራሽነት የመቀየርና በአዲስ የመተካት ፕሮጀክት እንደ ማዕበል ሆኖ የከተማችን ገላጭ የሆኑ አካባቢዎችን እንዳልነበሩ እያደረገ ቅርሶቻችንን እየበላ የብዙዎችን ሕይወት በማናወጥ ላይ ይገኛል ያለው ፓርቲው ይህ ድርጊት ሊቆም እንደደሚገባ አሳስቧል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው አዲስ አበባ ራሷን እንጂ ኒው ዮርክ፣ ሎንዶን፣ ቦነስአይረስ፣ ቶኪዮ፣ ናይሮቢ ወይም ዱባይን መሆን አትችልም መሆንም አይገባትም ብሏል።

አዲስ አበባ ለኗሪዎቿ ምቹ ለጎብኚዎቿ ደግሞ ሳቢና ማራኪ የምትሆነው ራሷን ሆና ስትገኝ ብቻ ነው ሲልም ገልፃል።

የሰራውን በነጋታው የሚያፈርሰው ከተማ አስተዳደሩ የሚያባክነው የሕዝብ ገንዘብ ነውና አሁንም ቆም ብሎ በማሰብ ቅርሶቻችን ተጠብቀው እንዲቆዩ፣ የቀደመ ማነንታችን መገለጫ አሻራዎቻችን ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብሏል።

“አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን” በሚል አማላይ ሀሳብ የዘመናዊ ህንጻ ግንባታ፣ ከተማና ከተሜነትን ለዘመናት ያስተዋወቀችውን የፒያሳ መንደር ማፍረስ በጥንታዊ መንደርነት ከልለን ማግኘት የምንችለውን የቱሪዝም ሀብት የሚያሳጣን ከመሆኑ ባሻገር፤ የመንግሥት የተንሸዋረረ እይታና ማንአለብኝነት ያመጣው ነው ብለን እናምናለን ሲል ገልፃል።

ፈረሳው በዚሁ ከቀጠለ የአዲስ አበባን መነሻ አሻራ ለማየት የምንቸገር ይሆናል ሲል የገለፀው ፓርቲው የቅርስ ባለስልጣን እና የቱሪዝም ሚኒሰቴርም ድርጊቱን የመመርመርና የማረም ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply