ወደ አዲስ አበባ የኋላ ታሪክ እንመለስ። የአዲስ አበባ የጥንት ስም በረራ ነው ብለናል። በረራም የኢትዮጵያ የነገስታቱ ዋና መቀመጫ በመሆን ከአጼ ዳዊት ቀዳማዊ (1380-1413) ጀምሮ እስከ አጼ ልብነ ድንግል (1508-1540) ከመቶ ዓመት በላይ አገልግላለች። በረራ ወረብ በሚባል አውራጃ ስር ትተዳደር እንደ ነበር የታሪክ መረጃዎች ያስረዳሉ። ወረብ ታላላቅ አብያተ ክርስትያናት እና ቤተ መንግስት የነበሩበት በጣም ሀብታም አውራጃ ነበር። በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ብዙ የውጭ አገሮችን የጎበኙት አባ ዳንኤል የተባሉ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወረብን በኢየሩሳሌም መስለው ጽፈዋል። በዚሁ ዘመን የግራኝ አህመድን ጦርነት የዘገበው ከሰራዊቱ ጋር በመሆን ወረብንና በረራን ያየው ሺሀብ አደዲን አህመድ ቢን አብደል ቃድር ቢን ሳሌም ቢን ኡትማን (Šihāb ad-Dīn Aḥmad bin Abd al-Qāder bin Sālem bin Uṯmān) ፉቱሕ አል-ሀበሻ (Futūḥ al-Ḥabaša ) በተሰኘው መጽሀፉ ወረብን የሀበሾች ምድራዊ ገነት ይላታል።