አዲስ አበባ በራሷ ግዛተ-መሬት ላይ የፌዴራል /ክልልነት/ መብት ሊረጋገጥላት ይገባል!

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር በመመዘኛዎቹ ላይ በኢትዮጵያ ተፃራሪ አቋም ባላቸው ልሂቃን ዘንድ ስምምነት ላይ ሊደርስ ቢችል፣ ፌዴራላዊ የመንግስት አደረጃጀት የፖለቲካ አለመግባባት መንስኤ ሊሆን የሚችል አልነበረም፡፡ ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ዋነኛ መገለጫ ሊሆን የበቃው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሊግባቡ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ሊግባቡ ያልቻሉበትም ምክንያት በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት የግንባታ ታሪክ ላይ ልዩነታቸውን ማጥበብ ባለመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ትውልድ ደግሞ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በ1940ዎቹ ዓመታት ተወልዶ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለዩኒቨርስቲ ደረጃ የደረሰው ትውልድ ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ1960ዎቹ ሁኔታ ደግሞ አለም በሁለት ተፃራሪ የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ጎራዎች ፉክክር ተቀስፋ ተይዛ የነበረችበት ወቅት ነበር፡፡ በ1960ዎቹ ለጉልምስና ከደረሰው ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ነው ባይባልም ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ አለኝ ብሎ ያቀነቅን የነበረው የትውልዱን የአመራር ሚና የተጫወተው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም አስተምህሮ የተቀበለው ነበር፡፡

ይሁንና የዚህ የ1960ዎቹ የተማሪ አብዮተኞች እና የነሱ ከፊል ውጤት ሆነው ያቆጠቆጡት የነገድ ድርጅት መሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ በተፃረረና ባልተገናዘበ ሁኔታ የሶቭየት ሕብረትን የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የስታሊንን “የብሔርና የቅኝ ግዛት ጥያቄ” መጽሐፍ ቃል በቃል በመገልበጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ችግር “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች መስተጋብር ነው” የሚል የሐሰት የታሪክ ትርክት ይዘው ተነሱ፡፡ እነዚህ ከተማሪ አብዮተኝነት ወደ ነገድ ድርጅትነት የተሸጋገሩት ከደርግ መንግስት ጋር ለ17 አመት ጦርነት አድርገው በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያላሰለሰ ድጋፍ በ1983 በኢትዮጵያ ጦር ላይ ድል ሊቀዳጁ በቁ፡፡ አነዚህ ሃይሎች በተጠናወታቸው “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች” የሃሰት ትርክት ውጤት የሆነውን የመገንጠል መብት ሕገ መንግስታዊ መብት ያደረገ፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ቋንቋን መሰረት ያደረገ መንግስታዊ የፌዴራል አወቃቀር በኢትዮጵያ ላይ አነበሩ፡፡
በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የጐሳና የዘረኝነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት የመንግስት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አደረጃጀት አይነተኛ መገለጫ ከመሆን አልፎ ይኸው አይነት አደረጃጀት ወደ እምነት ተቋማት ሳይቀር ዘልቆ እንዲገባ ተደረገ፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ በማይታወቅ ሁኔታ በተረኝነት መንፈስ የተቃኘ ተቋማዊ/መንግስታዊ ሙስና እና የፍትህ መዛባት የስርዓት መገለጫ ሊሆን በቃ፡፡ ከህዝቡ ታሪካዊ አሰራር ጋር ባልተገናዘቡ የክልል አደረጃጀቶች ምክንያት በሃገራችን እንግዳ በሆነ መልኩ ማንነትን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲበራከቱ፣ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው በፌዴራል መንግስቱና በክልል መንግስታት መካከል የሃላፊነትና የተጠያቂነት ጉዳይ አሻሚ በማድረግ፣ የአገሪቱ ብሔራዊ ስሜት እንዲላሽቅ በምትኩ ጠባብና ክልላዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ የዘውግ ፌዴራሊዝም ስርዓት ችግር ብሔረሰብን ዋነኛው የፌዴራል ስርዓቱና የአገር መንግስት ግንባታ መሰረት ማድረጉ ነው፡፡
እዛው ተወልዶ ያደገውና ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አንድ ብሔረሰብን እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን መሠረት አድርጎ በተዋቀረ ክልል ውስጥ አስገብቶ እንዲተዳደር ማድረግ ፍትሃዊነት የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ጥያቄ ከራሴ ውጭ በኔ እጣ ሌላ ሊወስንብኝ አይገባም የሚል ነው፡፡ አዲስ አባባ በኦሮሚያ ጆግራፊያዊ ክልል ውስጥ በመገኘቷ ብቻ ለአዲስ አበባ ባለቤትነት የመብት መብለጫ፣ ለተፈጠረ ውጥንቅጥ ደግሞ የአዲስ አበባ ህዝብን መብት ማሳነሻ ማድረግ በምንም መመዘኛ ተገቢነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡
የኢፌድሪ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 69 “የፌዴራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው ቢታወቅም የህወሓት እና የኦነግ በሆነው ሕገ መንግስት ውስጥ “በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ይኖረዋል” በሚል መካተቱ ችግሩን ሆን ተብሎ እንዲወሳሰብ አድርጎታል፡፡
በ1989 የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት አዲስ አበባ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር ሲደነገግ፣ በሕገ መንግስቱም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት የከተማዋ ስምና ስያሜ አዲስ አበባ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ይሁንና ቻርተሩን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቂ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጽደቅ ሂደቱ በደባ እንዲቀር ተደርጓል፡፡ አዲስ አበባ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ እና እንደ ካንቤራ የፌዴራል መንግስት ግዛት ናት የሚል የሕግ አንቀጽ የለም፡፡ ይህ አይደለም እንዳይባል በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር ጉዳይ በአዲስ አበባ የግዛት ክልል ውስጥ የተፈፀመ ወይም የተከናወነ የሕግ ጥሰት ግን ልክ የፌዴራል መንግስት ይዞታ አንደሆነችው ዋሽንግተን የመዳኘት ስልጣንን ለፌዴራል መንግስቱ ይሆን ዘንድ በሕግ ተለይቶ ተሰጥቷል፡፡ ማለትም በተግባር የፌዴራል መንግስቱ አዲስ አበባን እና ድሬደዋን የራሱ ግዛት አድርጓቸዋል፡፡
ሕገ መንግስቱ አዲስ አበባ እራሱን የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን የሰጠው መሆኑ ከላይ የተጠቀሰው የወንጀልና የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ለመዳኘት ከተሰጠው ስልጣን ጋር ሲዳመር አዲስ አበባ ልክ እንደ ዋሽንግተን የፌዴራል ግዛት እንደሆነች ለመረዳት ይቻላል፡፡ በተጨባጭ ግን አዲስ አበባ ከተማ የተተወላት የከተማ ነክ አስተደደርና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመዳኘት ስልጣን ነው፡፡ ማለትም ስለ ዳኘነት ሲሆን መሬቱ የፌዴራል መንግስት፣ ስለ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲሆን የከተማ መስተዳድሩ ሆኗል፡፡
አዲስ አበባ ራሷን የማስተዳደር መብት በሕገ መንግስቱ የታወቀ ቢሆንም፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ውክልና የላትም፡፡ ሕገ መንግስቱ ከሚደነገገው ውጭ ስትደዳደር የቆየችው በህወሓት/ኢህአዴግ፣ አሁን ደግሞ በኦህዴድ/ብልጽግና ነው፡፡ በሌሎች ክልሎች ክልሎችን የሚያስተዳድሩ የክልል ፓርቲዎች አሉ /ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ወዘተ…/ አዲስ አበባ ላይ ግን የሚወክላት የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ገዥ ፓርቲዎች ፍላጎታቸውን የሚጭኑባት ከተማ ናት፡፡ ቀደም ሲል ህወሓት/ኢህአዴግ አሁን ደግሞ ኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን ማስተዳደሩን ቀጥሎበታል፡፡ ይህ ሁኔታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ፍፁም የሚጥስ ነው፡፡
አዲስ አበባን እንዲመራ የሚመደበው በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከነበሩ ወይም ካሉ የክልል ገዢ ፓርቲዎች እንጂ በከተማው ሕዝብ ነፃ ምርጫ አልነበረም፡፡ አሁንም አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ቀደም ሲል ከሁለቱ ክልሎች /ትግራይ፣ ኦሮሚያ/ አሁን ከ “ለውጡ” ወዲህ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል በሚመጡ ተሹዋሚዎች እንድትደዳደር መደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥቅምና ፍላጎት እንዳይከበር ያደረገ የፖለቲካ ደባ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ከ7 ሚሊዮን የሚልቀውን የአዲስ

የአዲስ አበባ ንቅናቄ

Leave a Reply