”አዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በፍትሀዊነት ማሟላት ይገባዋል“:-ኢሰመጉ

ሐሙስ ሐምሌ 14 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አዲስ አበባ ከተማ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት በፍትሀዊነት ማሟላት ይገባዋል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አሳሰበ።

ኢሰመጉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 1 ቀን 2014 ለባለእድለኞች ያወጣውን የጋራ መኖሪያ ቤት እጣ አወጣጥ ሂደትና ሐምሌ 6 ቀን 2014 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውድቅ ማድረጉን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መግለጫ፤ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የ3ኛ ዙር የ40/60 እና 14ኛ ዙር 20/80 እጣ የተካተቱት በ1997 እና በ2005 ተመዝግበው እስከ የካቲት 2014 ድረስ በአማካይ ለ60 ወራት የቆጠቡ ሲሆኑ፤ በ20/80 መርሃ ግብር 18 ሺህ 648፣ በ40/60 መርሃ ግብር 6 ሺህ 843 ቤቶች በድምሩ 25 ሺህ 491 ቤቶች ለነዋሪዎች እንደሚወጣ ግልፆ እንደነበር አስታውሷል።

በተጨማሪም የእጣ ማውጫው መተግበሪያ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ መሆኑን፣ የፌደራልን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ይሁንታን ያገኘና በግል ተቋማት ታዛቢዎች ጭምር ታይቶ እንደተረጋገጠ መገለጹንና ሐምሌ 1 ቀን 2014 የ20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድለኞችን እጣ ማውጣቱ አስታውሷል።

ነገር ግን፤ ከእጣ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት በኋላ የተለያዩ ጥቆማዎች በመቅረባቸው፤ የተለያየ ተዓማኒነት ጉድለቶች በመታየታቸው የከተማ አስተዳደሩ ሐምሌ 6 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውድቅ ማድረጉን ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል የ20/80 ባለ ሥስት መኝታ ቤት እጣ ውስጥ ያልተካተተ መሆኑ ያስታወሰው ኢሰመጉ፤ ይህም ከ2005 ጀምሮ ለተከታታይ 9 ዓመታት ያህል ሳያቋርጡ በመቆጠብ ላይ ቢገኙም በ14ኛ ዙር እጣ ውስጥ ሳይካተት መቅረቱ ቅሬታን እንደፈጠረባቸው፤ በእጣው ተሳታፊ ያልሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች መግለጻቸውን ካሰባሰባቸው መረጃዎች ማወቅ መቻሉን ገልጿል፡፡

ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካለው ገቢ አንጻር፤ በ1997 እና 2005 ብቻ ሳይሆን ከዚያም በኋላ ምዝገባ በማካሄድ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ ሲገባው፤ በቀደመው አሰራር የነበረውን ኢ-ፍትሃዊ፣ ለዘረፋና ለማጭበርበር የተመቸ የእጣ አወጣጥ አሰራር የቀጠለ መሆኑን በተደጋጋሚ መታዘቡን ነው ኢሰመጉ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡

ስለዚህ ከዚህ አሰራር ራሱን በማረም በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶች ግልፀኝነትንና ፍትሃዊነትን በተከተለ ሁኔታ ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ እንዲያደርግም አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) የኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 90(1) የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ኹሉም ኢትዮጵያዊ የትምርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የንጹህ ውሀ፣ የመኖሪያ፣ የምግብና የማህበራዊ ዋስትና እንዲኖረው እንደሚደረግ መደንገጉን በመግለጽ፤ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀችው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫና፤ የሙስና ወንጀሎች አዋጅና ድንጋጌዎችን አጣቅሷል።

በዚህም መሰረት ኢሰመጉ:-

• የእጣ ማውጫው መተግበሪያ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ መሆኑን፣ የፌደራልን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ይሁንታን ያገኘና በግል ተቋማት ታዛቢዎች ጭምር ታይቶ እንደተረጋገጠ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገልጾ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ መጭበርበር የተፈጠረ ሲሆን፤ መንግስት ከዚህ በቂ ትምህርት በመውሰድ ቴክኖሎጂን አስመልክቶ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ፣

• መንግስት ዕጣ ለማውጣት ተጠቅሜበታለው ያለውን ሶፍትዋር መተግበርያ በገለልተኛ አካል እንዲያስመረምር እንዲሁም ለህዝብ ውጤቱን ይፋ እንዲያደርግ ፣

• በጉዳዩ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችና አመራሮች ላይ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ በህግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፣

• ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለሚገባቸው ሰዎች በአግባቡ እንዲያስተላልፍ እንዲሁም የዜጎችን በቂ የሆነ የኑሮ ደረጃ የመኖር መብትን እንዲያረጋግጥ፣

• በ14ኛ ዙር ያልተካተቱትን የ20/80 የባለ ሶስት መኝታ ቤት እድለኞችን መንግስት በአፋጣኝ ግልጽና ተአማኒ በሆነ መንገድ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ፤

• ለኢሰመጉ እየደረሱ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለያዩ ቦታዎች ከተከራዮች ተመላሽ የተደረጉ የመንግስት ቤቶች ያለአገልግሎት ታሽገው የተቀመጡ በመሆኑ ወደ አገልግሎት በማስገባት የነዋሪውን የቤት ችግር አስተዳደሩ እንዲፈታ፣

• የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት፣ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ጥፋተኛ ሆነው የተገኙትን በህግ ተጠያቂ በማድረግ መንግስት ያለበትን ሀላፊነት እንዲወጣ ኢሰመጉ ጥሪውን አቅርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply