አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት ከ7መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለማመንጨት ማቀዱን አስታወቀ፡፡ዩኒቨርሲቲዉ በሀምሌ ወር መጨረሻ በሚኒስትሮች ምክርቤት ራስ ገዝ እንዲሆን ደንብ እንደወጣለት…

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ዓመት ከ7መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለማመንጨት ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ በሀምሌ ወር መጨረሻ በሚኒስትሮች ምክርቤት ራስ ገዝ እንዲሆን ደንብ እንደወጣለት የሚታወስ ነዉ፡፡

ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር እያደረገ በሚገኘዉ ጉዞ ዉስጥ በዚህ ዓመት ከ7መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለማመንጨት ማቀዱን ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ዶክተር ሳሙዔል ክፍሌ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ከአንድ አመት እስከ አንድ አመት ተኩል ጊዜ ዉስጥ ራስ ገዝ ሆኖ መስራት እንደሚጀምር የገለጹት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ በዚህ የሽግግር ወቅት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉን አንስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ራስ ገዝ ለመሆን እያደረገ በሚገኘዉ የሽግግር ወቅት፤ ተቋሙ ስለሚተዳደርበት ስርዓት ፣ የተማሪ ቅበላ፣ የሰዉ ሃይል እና ሌሎች ጉዳዮች የሚተዳደሩበት የህግ ማዕቀፎችን የማዘጋጀት እና የማዉጣት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸዉ ተገልጿል፡፡

አንድ ዩኒቨርሲቲ ራስ ገዝ ሲሆን ከመንግስት የሚደረግ ድጋፍ ይቆማል ማለት አይደለም ያሉት ዶክተር ሳሙዔል ፤ድጋፉ ለተወሰኑ ዓመታት የሚቀጥል በጊዜ ሂደትም እየቀነሰ የሚሄድ እንጂ የሚቀር አለመሆኑን አንስተዋል፡፡

በዚህም ተቋሙ ከሚሰራቸዉ የተለያዩ ምርምሮች እና ተቋማዊ ስራዎች በዚህ ዓመት ከ7መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለማመንጨት መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ራስ ገዝ ይሆናል ሲባል የተለያዩ ብዥታዎች ተፈጥረዋል ያሉት ዶክተር ሳሙዔል ራስ ገዝ ይሆናል ማለት ተቋሙን ወደ ንግድ ስፍራ ለመቀየር አስበናል ማለት አይደለም ብለዋል፡፡

ከመጀመሪያ ድግሪ እና ከድህረ ምረቃ ተማሪዎች ከሚገኝ ክፍያ ከፍተኛ ሃብት ማግኘት አይቻልም ስለዚህ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን በመስራት የተለያዩ ገቢዎችን ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም ነዉ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ የገለጹት፡፡

ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲዉ ራሱን ችሎ ራስ ገዝ እስኪሆን ድረስ የተማሪ ቅበላ ባለበት የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዉ፤ሙሉ ለሙሉ ራስ ገዝ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ የተመረጡ እና ብቃት ያላቸዉ ተማሪዎች ብቻ የሚማሩበት ተቋም እንደሚሆን አስታዉቀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዉ ራስ ገዝ በሚሆንበት ወቅት ወደ ዩኒቨርሲቲዉ አልፈዉ ነገርግን ከፍለዉ መማር የማይችሉ ተማሪዎችን በመንግስት ስፖንሰር አድራጊነት ትምህርታቸዉን የሚቀጥሉበት አሰራር መኖሩንም ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ከመስከረም 1 ቀን 2016 ዓም ጀምሮ ከዚህ ቀደም ከተቋቋመዉ ቻንስለር እና ቦርድ በተጨማሪ ሽግግሩን የሚያግዙ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ተመድበዉ ስራ መጀመራቸዉም ተገልጿል፡፡

በእስከዳር ግርማ
መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube
https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/video

Source: Link to the Post

Leave a Reply