”አዳናዊት ይሄይስ ላይ የአስገድዶ መድፈር እና ግድያ ወንጀል ፈጽሟል በሚል በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ በጥንቃቄ እየተመራ ይገኛል”:-የፍትህ ሚኒስቴር

ግለሰቡ ሟችን የገደላት በዋስትና ከወጣ በኋላ ነው በሚል እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰተኛ ነው ተብሏል

ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) አዳናዊት ይሄይስ ላይ የአስገድዶ መድፈር እና ግድያ ወንጀል ፈጽሟል በሚል በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ በጥንቃቄ እየተመራ ይገኛል ሲል የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

እስካሁን በፖሊስ እና የዐቃቤ ሕግ የምርመራ ቡድን በተሰበሰበው ማስረጃ መሰረት፤ ተጠርጣሪው ሚካዔል ሽመልስ ሟች አዳናዊት ይሄይስ ላይ ከ10 ዓመቷ ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈጽምባት እንደቆየ እና ሟች እድሜዋ 17 ዓመት እስኪደርስም ድረስ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽምባት ቆይቶ መስከረም 14 ቀን 2015 ድርጊቱን ሲፈጽም ያየው ሰው ለእናቷ በተናገረው መሰረት ጥቆማው ለፖሊስ ማድረሱ ተገልጿል፡፡

ፖሊስም በአስገድዶ መድፈር ወንጀል የጠረጠረውን ይህንኑ ግለሰብ ለመያዝ እንዲችል ከፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ወደ መኖሪያ ቤቱ የሄደ ሲሆን፤ ይሁንና ተጠርጣሪው የፖሊሶችን መምጣት ያውቅ ነበርና አስቀድሞ ከአካባቢው ይርቃል።

በዚህም ምክንያት ፖሊስ ወደ መጣበት ተመልሶ በሌላ መንገድ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል፡፡

ከሰዓታት በኋላ ተጠርጣሪው ከሄደበት ተመልሶ ሟች ከእናቷ ጋር እንዳለች “ለፖሊስ የጠቆምሽው እና ያዋረድሽኝ አንቺ ነሽ” በማለት በስለት ወግቶ እንደገደላት እና ወደ ቤቱ ተመልሶ ልብሱን በመቀየር ሊያመልጥ ሲል በአካባቢው ህብረተሰብ ሊያዝ እንደቻለ ያስረዳል፡፡

ፖሊስ እና በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በአሁኑ ጊዜ ምርመራቸውን በማጠናቀቅ ክስ መስርቶ በህግ ለማስጠየቅ በሚያስችል ሁኔታ ላይ በጥንቃቄ እየሰሩ እንደሚገኝ ተገለጸ ሲሆን፤ ግለሰቡ ሟችን የገደላት በዋስትና ከወጣ በኋላ ነው በሚል በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑንም የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል።

The post ”አዳናዊት ይሄይስ ላይ የአስገድዶ መድፈር እና ግድያ ወንጀል ፈጽሟል በሚል በተጠረጠረው ግለሰብ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ በጥንቃቄ እየተመራ ይገኛል”:-የፍትህ ሚኒስቴር first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply