አዳዲስ የእዝ ማእከሎች በትግራይ የፈጠሩት የፖለቲካ ትኩሳት

በጥቅምት የመጀመሪያው ሳምንት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ‘’የሚሰጠኝን ግዳጅ በፍጥነት ለመከወን ያስችሉኛል’’ ያላቸውን ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ እዞችን አዋቅሯል። እነዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋቀሩ አዲስ እዞች ‘’ሰሜን ምዕራብ ዕዝ’’ እና ‘’ማእከላዊ እዝ’’  ሲሆኑ የእዝ ማእከላቸው በቅደም ተከተል ባህር ዳር እና አዲስ አበባ እንደሆነ ይፋ ተደርጓል።

ነባሮቹ ሰሜን፣ ምዕራብ፣ ደቡብ እና ምስራቅ እዞች እንዳሉ ሆነው፣ ተጨማሪ የማእከል እና ሰሜን ምዕራብ እዞች ሲዋቀሩ፣ ምን ተልእኮ ይኖራቸዋል፣ ለምንስ አሁን ማዋቀር ተፈለገ፣ የተኛው አከባቢ ይሸፍናሉ፣ ከየትኛው እዝ ተውጣጥተው  የተዋቀሩ ናቸው፣ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ማጫሩ አልቀረም።

ከዚህ በተጨማሪ መቐለ ከሚገኘው የሰሜን እዝ የሎጂስቲክስ እንቅስቃሴ እና የአመራር ለውጥ መደረጉን ተሰምቷል። ሰሜን እዝ ከለውጥ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ አዛዥ ሲቀየርለትም ታይቷል።

በትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና በፌደራል መንግስት መካከል ለተፈጠረው መቃቃር ይህ ተጨማሪ ችግር እንደሆነ እየተስተዋለ ነው። የፌደራል መንግስት ‘’የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን’’ ለመመከት የተቋቋሙ እዞች ናቸው ሲል፣ የትግራይ መንግስት ደግሞ ‘’የትኛው የውጭ ሃይል ነው፣ የውስጥ ጠላቱስ ማነው’’ ሲል በጥርጣሬ አይቶታል። ወታደራዊ ቁሳቁስ ማንቀሳቀስ እና ሹምሽር ማካሄድ እንደማይቻልም የክልሉ መንግስት ከሰሞኑ የአቋም መግለጫው ይፋ አድርጓል።

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እንደዛ ለማለት የሚያስችል ስልጣን አለዉ ወይ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል፣ መልሱ ወደ ሌላ ምክንያት ይወስዳቸኋል። ብዙ ሰው እንደሚረዳው ከኢህአዴግ መፍረስ በኋላ በህወሓት እና በብልፅግና የነበረው ልዩነት አድጎ በፌደራል እና በክልሉ መንግስታት ደረጃ የሚገለፅ ሆነዋል።

ብልፅግና የሚባል አንድ ‘’ውሁድ’’ ፓርቲ ሲመሰረት፣ ህወሓት ምክንያቶቹን ጠቅሶ ብልፅግና ውስጥ አልገባም ሲል በአቋሙ ፀና። ብልፅግና ደግሞ ‘’ካልተቀላቀልከን ትጠፋታለህ’’ ዓይነት የፖለቲካ መንገድ ተከተለ። ህወሓት በበኩሉ ብልፅግናን ‘’ኢትዮጵያን ማስተዳደር የማይገባው አሃዳዊ ሃይል፣ ግልገል አንባገነን፣ የሀገር ሉኣላዊነት አሳልፎ የሰጠ’’ ሲለ ሰርክ መግለፁን ተያያዘው። ህወሓት ትግራይን በብዙ ፈተና ውስጥ ሆኖ፣ ነገር ግን ያለ ብልፅግና ጣልቃ ገብነት እያስተዳደረ አቅሙን ሲያጠናክር ቆየ።

በዚህ መሃል የምርጫ ጉዳይ መጣ። የፌደራል መንግስት የኮቪድ-19 ወረረሽን እንደምክንያት ጠቅሶ ምርጫ መራዘም አለበት ሲል፣ ህወሓት ደግሞ  ህገ-መንግስቱ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መካሄድ አለበት ሲል ወሰነ። የፌደራል መንግስት ለነሓሴ 2012 ዓ/ም ይካሄዳል ብሎት የነበረ ምርጫ፣ ህገ-መንግስታዊ ትርጉም በማሰጠት እንደገና ሲያራዝም፣ ህወሓትና የትግራይ ክልል መንግስት ደግሞ በተቃራኒው ክልላዊ የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም 04 ጳጉሜ 2012 ዓ/ም ትግራይ ውስጥ ለክልሉ ምክር ቤት ምርጫ ተካሄደ። እስካሁን  እንደመበሻሸቅ ሲወሰድ የነበረ መሳሳብ ከምር መሆኑን ታየ፣ በሁለቱ መካከል የነበረ ስንጥቅም ሰፋ።

ምርጫ ማካሄድ በትግራይ በኩል ህገ-መንግስት የማክበር፣ ራስን በራስ የመወሰን እና የማስተዳደር መብት ተደርጎ ሲወሰድ፣ በአንፃሩ በፌደራል መንግስት ምርጫ ማራዘም ለጤና እና መረጋጋት ሲባል የግድ ነው ተባለ። በኮቪድ ጫና እና በመከበብ ስሜት ውስጥ የተካሄደው የትግራይ ክልል ምርጫ፣ ‘’የጨረባ ምርጫ ነው፣ ህገ-ወጥ ነው፣ እውቅና የለዉም’’ ሲል ፊደራል መንግስት ኮነነ። የትግራይ ክልል መንግስት በበኩሉ ‘’ኢትዮጵያ ባልተመረጠ መንግስት መመራት የለባትም፣ አሁን ስልጣን ላይ ያለው የመንግስትን የተቆጣጠረው ቡድን ቅቡልነት የለዉም፣ ህጋዊ አይደለም፣ ከመስከረም 25 በኋላ የሚያወጣቸውን ህጎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ ውሳኔዎች፣ የሚፈፅማቸው ስምምነቶች ተፈፃሚነት የላቸውም’’ ሲል ገለፀ። 

ስለዚህ የከሰሞኑ የትግራይ ክልል መግለጫ እና ከፌደራል መንግስት ያለውን እሰጥአገባ በአንድ በኩል ‘’የስልጣን ዕድሜው የጨረሰ፣ ህገ-ወጥ የሆነ የፌደራል መንግስት የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት መዋቅር መቀየር አይችልም፣ ሎጂስቲክስ ማንቀሳቀስ የለበትም’’  የሚል መነሻ ያለው ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ የሰሜን ምዕራብ እዝ አደረጃጀት አብዛኛው የአማራ ክልል እስከ ሰሜናዊው ምዕራብና ምዕራብ ትግራይ ዞኖች [ተከዘ ወንዝንና ሑሞራን ጨምሮ] በእዙ ስር ለማድረግ ያለመ፣ በሴራ የተሞላ፣ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትን የማያከብር ውሳኔ ያለበት ነው’’ ሲል የትግራይ ፖለቲከኞች ይከሳሉ። ይሀ ለምን አስፈለገ ሲሉም ይጠይቃሉ?  

በትግራይ ፖለቲካ የሚነሳው ሌላ ስጋት ይህ የፌደራል መንግስት ውሳኔ ሰሜን እዝን ለሁለት በመክፈል የጦር መሳሪያና የሰው ሃይል ከድንበር በማሸሽ ሀገርን ሊያስጠቃ የሚችል እንዲሁም ባህር ዳር በቀጥታ ከኤርትራ በማገናኘት ብልፅግና እና ሻዕቢያ በቀላሉ የሚመላለሱበት ኮሪደር ለመፍጠር የተሸረበ የፖለቲካ ሴራ ነው የሚል ነው። 

ከዛም በላይ አዲሱ የሰሜን ምዕራብ እዝ ማደራጀት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት እንደ ወልቃይት አስመላሽ ኮሚቴ
ያሉትን የትግራይ ክልል መንግስት ‘’የግዛት ተስፋፊዎች እና ትምክተኞች’’ ብሎ የሚጠራቸው የፖለቲካ ቡድኖች ጥያቄ በወታደራዊ መመሪያ መልስ ለመስጠት ነው፣ ይላሉ በትግራይ በኩል ሂደቱን ባይነ ቁራኛ የሚከታተሉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች።

በሌላ በኩል ‘’ማእከላዊ እዝ” ተብሎ የተቋቋመውና በአዲስ አበባ ዋና መምሪያ ስር በደሴ ከተማ ቀዳማይ መምሪያ በማድረግ ደቡብ ትግራይን በአደረጃጀትም በወታደራዊ እዝም ወደ አማራ ክልል ለማስገባት የታቀደ ነው። በዚሁ ኦፕሬሽን ራሳቸውን በተለያየ የኮሚቴዎች ስም የሚጠሩ የርስት ፖለቲካ አቀንቃኞችን ጥያቄ ለመደገፍ ነው የሚል
መላምት ቢኖርም፣ በዋነኛነት ግን አዲስ አበባ በዙሪያዋ ሊነሱባት ከሚችሉ አመፆች ለመከላከል እና ፌደራል መንግስቱን ለመተበቅ እንደሆነ
ይገመታል።

እነዚህ የወታደራዊ አደረጃጀቶች እና እንቅስቃሴዎች መንግስት እንደሚለው የውጭ ጠላት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው ለውስጥ ጉዳይ ትኩረት የሰጡ እና ፖለቲካዊ ተልእኮ የሚጫናቸው እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።

ሀገር ተክለብርሃን

አውሎ ሚዲያ

20 ጥቅምት 2013 ዓ/ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply