
አፈና የተፈጸመበት የአለርት ሆስፒታል ሳይካትሪስት አድራሻ በትክክል ሳይታወቅ 10 ቀን ሆኖታል፤ ባለቤቱም አፋልጉኝ ስትል ጥሪ አድርጋለች። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 9/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ አዲስ አበባን ጨምሮ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የአማራ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችንስ የማህበረሰብ አንቂዎችን እና ሌሎችንም በማሰር ግፍ እየፈጸመ ነው በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ እየቀረበበት ነው። በአስቸኳይ እንዲፈታም ከተለያዩ ወገኖች ጥሪ እየተደረገ መሆኑም ይታወቃል። ከሰሞኑ በአዲስ አበበ ከተማ በጸጥታ አካላት ታፍነው ትክክለኛ አድራሻቸው ባለመታወቁ በተለይም በቤተሰብ በኩል ከፍተኛ ጭንቀት እያጋጠመ መሆኑ ይታወቃል። ታፍነው አድራሻቸው ካልታወቁት መካከልም አብርሃም መልካሙ፣ አወቀ ስንሻው እና ኤርሚያስ መኩሪያ ይጠቀሳሉ። ከታፈነ 10 ቀን የሆነው የአለርት ሆስፒታል ሳይካትሪስት ባለቤቴን የአብርሃም መልካሙን አድራሻ አፋልጉኝ ስትል ጥሪ ያደረገችው በእምነት ቻላቸው ትባላለች። በአዲስ አበባ ዙሪያ ባለ ገዳም የልደታን በዓል ለማክበር ከመኖሪያ አካባቢው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሰፈራ የወጣው አብርሃም መልካሙ ከታፈነበት ሰኞ ሚያዝያ 30/2015 ጀምሮ እስከ ግንቦት 7/2015 ለ 8 ቀናት ያክል ትክክለኛ አድራሻው አልታወቀም ያለችው በእምነት ነገር ግን እሷ በሌለችበት ግንቦት 4/2015 አርብ ረፋድ ላይ በ3 የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በለበሱ አካላት ታጅቦ ከመጣ በኋላ ቤቱ ስለመፈተሹ እና ምንም ነገር እንዳልተገኘበት ገልጻለች። በፍተሻ ወቅትም አብርሃም መልካሙ በመሃል “ሳሸምንቱን ኤሁሉ አሽጋችሁኝ ነው የሰነበታችሁ” ስለማለቱ እና “እሱን እዚጋ ልንነጋገር አይደለም የመጣነው” የሚል ምላሽ ከአንደኛው አባል እንደተነገረው የጠቆመችው ባለቤቱ ጎረቤቶችቛ የት ነው የምትወስዱት አድራሻውን ንገሩን ቢሉም አልፈቀዱም ብላለች። በእምነት ቻላቸው ግንቦት 7/2015 ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ሄዳ ብትጠይቅም እዚህ የለም ስለመባሏ በመናገር የአፋልጉኝ ጥሪ አቅርባለች። በተመሳሳይ ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ሲመለሱ በታጠቁ ኦነጋዊያን ታፍነው ደብዛቸው ለጠፋው 17 የአማራ ተማሪዎች ያለመሰልቸት ድምፅ መሆኑ የተመሰከረለት ኤርሚያስ መኩሪያም ከታፈነ 4 ቀን ሆኖታል፤ አድራሻው ያልተነገረው ቤተሰብም በከፍተኛ ጭንቀት ላይ መሆኑ ታውቋል። በተያያዘ አቶ አወቀ ስንሻው በአዲስ አበባ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛ አመራርነት እና የፍኖት አሶሴሽን ዋና መስራችና ፕሬዝዳንትም ከመኖሪያ ቤቱ በአብነት አካባቢ በደህንነቶችና በበርካታ ፌደራል ፖሊስ ታፍኖ ወደ አልታወቀ ቦታ ከተወሰደ ከአንድ ሳምንት በላይ ሆኖታል፤ ቤተሰብም በጭንቀት ላይ ስለመሆኑ ተሰምቷል። እነ አብርሃም መልካሙ፣ እነ አወቀ ስንሻው እና እነ ኤርሚያስ መኩሪያ የት ናቸው? ብለው በመጠየቅ ብዙዎች የአገዛዙን የአፈና አካሄድ እያወገዙ ነው።
Source: Link to the Post