‹‹አፍሪካ ለአፍካዊያን›› የተሰኘ ዝግጅት ከጥቅምት 11 እስከ 13/2015 መዘጋጀቱ ተገለጸ

በመስቀል አደባባይና በወዳጅነት ፓርክ በሚካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ 55ቱም ኤምባሲዎች እንደሚገኙ ተነግሯል

ማክሰኞ ጷግሜ 1 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢዩዳን ሚዲያ ኃላ/የተ/የግል ማህበር ‹‹አፍሪካ ለአፍሪካዊያን›› የተሰኘና አፍሪካን በአፍሪካ ምርቶች፤ የባህል ኪነ ጥበብ እና ሌሎች በአይነትና በይዘት ለየት ያሉ አህጉራዊ ፕሮግራሞችን ከጥቅምት 11 እስከ 13/2015 ለማዘጋጀት ዝግጅቱን ማጠማቀቁን አስታውቋል፡፡

በዛሬው ዕለት በአምባሳደር ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ንግግር ያደረጉት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ዳንኤል ጥሩነህ፤ በዝግጅቱ የ55 አፍሪካ አገራት አምባሳደሮች እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡

የዝግጅቱ ዓላማ ትልቁን የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ነውም ብለዋል፡፡ በአህጉራዊ ዝግጅቱ አፍሪካ ሕብረት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እንዱሁም የቱሪዝም ሚኒስቴር ይገኙበታል ያሉ ሲሆን፤ ፕሮግራሙም በመስቀል አደባባይና በወዳጅነት ፓርክ እንደሚካሄድ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

በዚህም ከኤምባሲዎችና እና አፍሪካዊያን ምሁራን በሚደረግ ውይይት የልምድ ልውውጥ ይደረጋል ነው የተባለው፡፡

የኢኮኖሚና ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር ከሚካሄዱ ልየልዩ አህጉራዊ ጥረቶች ጋር የሚያያዝ ነው የተባለው ዝግጅቱ፤ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል ተስፋ እንደተጣለበት ተጠቅሷል፡፡

በተጨማሪም የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ባህሎቻቸውን የሚያንጸባርቁበት፤ የዳንስና የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የፋሽን፣ የእግር ኳስ ሾው እና ሌሎች ኹነቶች ይካሄዱበታል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ሌሎች ወደ 28 የሚጠጉ አንጋፋ ተቋማት እና አራት ታዋቂ አርቲስቶች እንደሚገኙ ዳንኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው የተገኙት የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች መሰረት አዛገ በፕሮግራሙ መዘጋጀት ደስታቸውን ገልጸው፤ የበጎ አድራጎትን ሥራ ሌሎች የአፍሪካ አገራትና እናቶች እንደ ሞዴል ወስደው እንዲሰሩ እናሳያለን ብለዋል፡፡

የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ በዚህ ዓመት በከፋ በችግር ላይ መንገድ ዳር ወድቀው የነበሩ 834 ሰዎችን እንዳነሱ ገልጸዋል፡፡ መሰረት አሁንም ቢሆን በርካታ እናቶች በየጎዳናው ወድቀው እንደሚገኙ እና ድርጅቱ ያነሳቸው ሰዎችም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply