አፍሪካ ቴሌሚድስን ኔትወርክ የጤናውን ዘርፍ በዲጂታል የሚያስተሳስር አገልግሎት በይፋ አስጀመረ

በአህጉሪቱ ያሉትን የጤና ባለሙያዎችን በአንድ ጥላ ስር በዲጂታል የጤና ኔትወርክ ማስተሳሰር ያስችላል የተባለለት ይኸው አገልግሎት   አሜሪካን ውስጥ የተጀመረ ሲሆን ሁሉም የአፍሪካ ሃገራት የራሳቸውን ቴሌሜዲስን ኔትወርክ በተናጠል ፤ ብሎም በአህጉሪቱ ስር ያሉትን ደግሞ በአንድ ጥላ የሚተሳሰሩበትን የዲጂታል አሰራርን ይዞ መጥቷል።

ዜጎች ከየትኛውም የአህጉሪቱ ክፍል፤ ገጠራማውን አካባቢ ጨምሮ ማንኛውንም አይነት ህክምና በሚያሻቸው ወቅት ካሉበት ሆነው፥ ስልካቸው ላይ በሚጭኑት በሞባይል መተግበሪያ የሚያሻቸውን የጤና ባለሙያዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ብቻ የማግኘት፣ የማማከር እንደ አስፈላጊነቱም ቀጠሮ የማስያዝ ብሎም ለአግልግሎት የሚያስወጣቸውን ክፍያ በ online የክፍያ ስርዓት ዝርጋታ መፈፀም የሚያስችላቸው መሆኑን በገለፃው ይፋ ተደርጓል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶር. ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በ 2020 እ.አ. ሀገሪቱን ወደ ዲጂታሉ አለም በይበልጥ ለማስገባት አላማ አድርጋ ከምትሰራቸው ስራዎች ጋር ተያያዥነት እንዳለው ገልፀው፤ ቴሌሜዲስን አፍሪካ ውስጥ ላሉ ኋላ ቀር ሃገሮች ብዙ እንቅፋቶችን ከማስወገድ አንፃር ያለውን አዎንታዊ ፋይዳ በስፋት አብራርተዋል።

የአሜሪካ ሚዲካል ሴንተር  ባለቤት ዶ/ ር አከዘ ጣዕመ  የህክምና ባለሙያዎች በቁጥር እጅግ አናሳ መሆናቸውን ግልፅ አድርገው፤ አሁን ላይ ባለን የህክምና ባለሙያዎች አቅርቦት ስሌት የዓለምን ህዝብ የጤና ሽፋን ለማዳረስ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች ሶስት መቶ አመታታ እንደሚፈጅባቸው እና በዛው ልክ ደግሞ እጅግ እየፈጠነ ያለው የህዝብ ብዛት ይህንን ስሌት እጅግ እንደሚያወሳስበው ብሎም መፍትሄም እንደማያመጣ አስረድተዋል። ከመመጣጠን የዘለለ ችግር ያለበትን የህክምና ባለሙያዎችና ህክምና የሚያሻቸው ህዝቦችን ተደራሽ ለማድረግ ቴሌ ሜዲስን ፕላትፎርም ፋና ወጊ ተስፋ ነው ብለዋል።

ታካሚውና የህክምና ባለሙያው አካላዊ መገኘት ሳያሻቸው በ አርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ በመታገዝ ማንኛውንም አይነት ህክምና ሰዎች ሆስፒታል መምጣት ሳያሻቸው የሚታከሙበት ፕላትፎርም ነውና ለህክምናው ዘርፍ የገዘፈ ስኬት ነው ብለዋል።

The post አፍሪካ ቴሌሚድስን ኔትወርክ የጤናውን ዘርፍ በዲጂታል የሚያስተሳስር አገልግሎት በይፋ አስጀመረ appeared first on Fidel Post.

Source: Link to the Post

Leave a Reply