አፍሪካ ቴሌሜዲሲን ኔትዎርክ የተባለ ዲጅታል የጤና አገልግሎት ተቋም በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል፡፡በሃገራችን ያለውን የህክምና አሰጣጥና ተደራሽነት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የተነገረ…

አፍሪካ ቴሌሜዲሲን ኔትዎርክ የተባለ ዲጅታል የጤና አገልግሎት ተቋም በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል፡፡

በሃገራችን ያለውን የህክምና አሰጣጥና ተደራሽነት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የተነገረለት አፍሪካን ሜዲሲን ኔትዎርክ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተገኙበት ነው በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው፡፡

የአፍሪካ ቴሌሚድስን ኔትወርክ መስራች የሆኑት ዶ/ር አከዛ ጣዕመ፣ሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነ አህጉራችን አፍሪካ ወደ ዲጂታል የጤና አገልግሎት እየገቡ መሆኑን ገልጸው፣ይህን በተቀናጀና በአንድ ጥላ ስር አሰባስቦ የተሻለ ስራ ለመስራት በማሰብ አፍሪካ ቴሌሜዲስን ኔትዎርክ መመስረቱን አብራርተዋል፡፡

በዚህ ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ እያንዳንዱ ሀገር የራሱን የቴሌ ሜዲስን በመፍጠር እንደየአካባቢያቸው ተጨባጭ ሁኔታ የጤና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዶ/ር አከዛ ማብራሪያ ቴሌሜድስን የጤና አገልግሎቶችን፣ በቴክኖሎጅ በመታገዝ በርቀት የሚሰጥ የህክምና ስርዓት ሲሆን፤ በዚህ አገልግሎት ውስጥ፣ ቴሌራዲዮሎጅ፣ ቴሌፓቶሎጅ፣ ቴሌፓርማሲ፣ ቴሌካድሮሎጅና ሌሎችም የህክምና አገልግሎቶችም የመሰጡበት አሰራር ነው፡፡

ይህን ስራ ሊሰራ የሚችል ሃባሪ ዶክ የተባለ የቴሌሜዲስን አፕም አብሮ ይፋ መደረጉን ዶ/ር አከዛ ተናግረዋል፡፡

የህክምና አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎችን፣ ስልካቸው ላይ በሚጭኑት የሞባይል መተግበሪያ የሚያሻቸውን የጤና ባለሙያዎች በኢንተርኔት አማካኝነት የማግኘት፣ የማማከር እንደ አስፈላጊነቱም ቀጠሮ የማስያዝ ብሎም ለአግልግሎት የሚያስወጣቸውን ክፍያ በኦንላይን የክፍያ ስርዓት መፈጽም የሚያስችል የዲጂታል አገልግሎት መሆኑንም ዶ/ር አከዛ አብራርተዋል፡፡

አገልግሎቱ በተለይም የህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እያገኘ ያልሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግና ታካሚው የሚያባክነውን የጊዜ፣የጉልበትና አላስፈላጊ ወጭ ይታደገዋል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣በስፔሽያሊስት ሃኪሞች የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የዲጅታል የህክምና አገልግሎት መስፋፋት የግድ አስፈላጊ መሀኑን ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ሃገርም የዲጅታል የህክምና አገልግሎትን ለማስፋፋት የ10 እቅዱ ላይ ትኩረት እንደተሰጠው የተናገሩት ሚንስትሯ፣በዚህ ላይ የግሉ ዘርፍም ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡

የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ አካባቢዎችን በዲጅታል የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ከተቻለ ከፍተኛ ስኬት መሆኑንም ሚንስትሯ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ታህሳስ 07 ቀን 2015 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply