አፍሪካ የራሷን የምግብ ፖሊሲ በማዘጋጀት ሂደት ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ

ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) አፍሪካ የራሷ የሆነ የምግብ ፖሊሲ እንዲኖራት የሚያስችሉ አስፈላጊ ሰነዶች ተዘጋጅተው ለአፍሪካ ህብረት እንደገቡና ሰነዶቹም በህብረቱ በኩል እየታዩ እንደሚገኙ የአፍሪካ የምግብ ሉአላዊነት ህብረት (Alliance for food sovereignty in Africa) “AFSA” የተሰኘው አህጉራዊ ተቋም አስታወቀ።

ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ የግብርና መንገድ (Agroecology) ላይ ትኩረቱን ያደረገ አህጉራዊ እና አለም አቀፍ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል መካሄድ ጀምሯል።

ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፤ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የአህጉራዊ ኢኮኖሚክ ምክር ቤት አባላት፣ ከ32 አገራት የተውጣጡ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ የግብርና መንገድ ላይ ትኩረት ያደረጉ የሥራ ፈጣሪዎችና በዘርፉ እየሠሩ የሚገኙ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተውበታል።

የጉባኤው አዘጋጅ የአፍሪካ የምግብ ሉአላዊነት ህብረት (AFSA) ዋና አስተበባሪ የሆኑት ዶ/ር ሚሊዮን በላይ፤ ”አፍሪካ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ ልትከተለው የሚገባው መንገድ ኬሚካል እና የአፈር ማዳበሪያን ብቻ መጠቀም ሳይሆን፤ ተፈጥሮ ላይ መሠረት ያደረገ መሆን ይገባዋል“ ያሉ ሲሆን፤ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ አፍሪካ የራሷን የምግብ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት፤ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ይረዳ ዘንድ አስፈላጊ ሰነዶች ተዘጋጅተው ለአፍሪካ ህብረት መግባታቸውን የገለጹት ዶ/ር ሚሊዮን፤ ሰነዶቹ በህብረቱ በኩል እየታዩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ የግብርና መንገድ መከተልን የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ ለአፍሪካ እንደሚያስፈልግ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያነሱት አስተበባሪው፤ በቅርቡ ካሜሮን ላይ ይህ ፖሊሲ እንዲጸድቅ የሚያበረታታና ህብረቱን የሚገፋፋ ትልቅ ስብሰባ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በዚህም በአፍሪካ የምግብ ሥርዓትን የመለወጥና የማደራጀት ማዕቀፍ ላይ፤ በአፍሪካ ውስጥ የሚፈልገውን አይነት የምግብ ሥርዓት እንዴት እውን ማድረግ ይቻላል፣ በብሔራዊ የምግብ እና የእርሻ ፖሊሲ ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ወጥ እና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው፤ እንዲሁም በአፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ጠንካራ ምግብ መሠረት ለመገንባት የሚያስፈልጉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው የሚሉ ጉዳዮች መነሳታቸውን አስረድተዋል።

“በአፍሪካ ብዙ በማምረት አፍሪካን መመገብ የሚሉ ብዙ ፖሊሲዎች አሉን“ ያሉት ዶ/ር ሚሊዮን፤ ነገር ግን ምርት ላይ ብቻ ማተኮር ለውጥ ሊያመጣ አይችልም። የህብረተሰቡ ጤና መጠበቅ አለበት፣ አካባቢንም የበለጠ ማጎሳቆል የለብንም ብለዋል።

መፍትሄውም አፈርን መመገብ መሆኑንም በማንሳት፤ መሬት ላይ ብዛት ያላቸው አዝርቶችን መትከል፣ የገበሬውን ዕውቀትና የሳይንሱን ዕውቀት ማቀናጀት እንዲሁም የማምረት ሂደቱ አካባቢያችንን በማይበክል ሁኔታእንዲሆን ማድረግ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።የአፍሪካ የምግብ ሉአላዊነት ህብረት (AFSA) በአብዛኛው በሌሎች አገሮች የሚቀረጸውና የሚመራውን የአፍሪካ አጀንዳ በማስቀረት አፍሪካ የራሷ የሆኑና ከከባቢ አየር ሁኔታዋ ጋር የሚስማሙ አጀንዶች እንዲኖሯት ለማስቻል መቋቋሙን ያነሱት የተቋሙ ዋና አስተባባሪ፤ ዛሬ በተጀመረው ጉባዔ ላይ የተገኙት አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎችም ግብፅ በቀጣይ በምታዘጋጀው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 27) ላይ ተሳታፊ እንደሆኑና እዛም ላይ አጀንዳቸውን አቀናጅተው በአንድ በማቅረብ ግልጽ የሆነ የአቋም መግለጫ እንደሚያወጡም አስረድተዋል።የአፍሪካ የምግብ ሉአላዊነት ህብረት (Alliance for food sovereignty in Africa) “AFSA” የተሰኘው አህጉራዊ ተቋም እ.ኤ.አ በ2009 በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ የተቋቋመና በአፍሪካ ተፈጥሮን መሠረት ባደረገ የግብርና መንገድ (Agroecology) ዙሪያ በመሥራት ላይ የሚገኝ አህጉራዊ ተቋም ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply