ኢመደአ ከ91 በላይ የሚሆኑ በሳይበር እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን አዳዲስ ታዳጊ ወጣቶችን መቀበሉን አስታወቀ

ዕረቡ ሐምሌ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል በ2014 የክረምት መርሃ ግብር ከ91 በላይ የሚሆኑ በሳይበር እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶችን ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተቀብሎ የሥልጠና ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡

የማዕከሉ ሀላፊ ካሳሁን ደሳለኝ እንዳሉት፤ የክረምት ወቅት ትምህርት የሚዘጋበት ጊዜ በመሆኑ በርካታ ተማሪዎች በመስኩ ካላቸው ልዩ ተሰጥዖ አኳያ በታለንት ማዕከሉ ተቀብለን የሥልጠና ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ከ6ኛ ክፍል ጀምሮ ከ91 በላይ ተማሪዎች በ2014 የክረምት ወቅት የተቀበላቸውን ጨምሮ ለአራት ዙር ያክል 127 ወንዶች እና 14 ሴቶች በጥቅሉ 141 ባለ ልዩ ተሰጥዖ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት ቴክኒካል ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑም ካሳሁን አስታውቀዋል፡፡

የሳይበር ታለንት ልማት ማዕከሉ የተቀበላቸውን ታዳጊ ወጣቶች ከክህሎት ስልጠናዎች ጀምሮ የቴክኒክ እና ለሥራቸው የሚጠቀሙባቸውን ቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሚሰሯቸውን የጥናትና ምርምር ሥራዎች ለመፈተሽና ለመሞከር የሚያስችላቸው ላብራቶሪም በማዕከሉ ውስጥ እንደሚያገኝ ሀላፊው አብራርተዋል፡፡

በተለያየ ምክንያት ወደ ተቋሙ የታለንት ማዕከል ላልመጡ እና በመስኩ ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን በተመለከተም የቀጥታ መረብ (Online) ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው ብለዋል።

ተማሪዎች የሚመረጡበት ወይም የሚመለመሉበት መስፈርትም ባዘጋጁት ፕሮጀከት መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

ማዕከሉ በቀጣይም አብዛኛውን ተሰጥኦ ያላቸውን ተማሪዎች የቀጥታ ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ሀላፊው አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮ ሳይበር ታለንት ልማት ማዕከል በሳይበር ሴኪዩሪቲ እና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ተሰጥዖ ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች ክህሎታቸውን ለማሳደግ እና ፕሮጀክቶቻቸውን ለመተግበር የሚያስችል የባለሙያ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተጠቁሟል።

አሁንም ፍላጎት እና ተሰጥዖ ያላቸው ታዳጊዎች እና ወጣቶች በ cychalleng.insa.gov.et ድረ-ገጽ መመዝገብ እንደሚችሉ እንዲሁም ለበለጠ ማብራሪያ በ 0904311833 ወይም 0904311837 መደወል እንደሚችሉ ሀላፊው ገልጸዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply