ኢሰመኮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው ውጥረት እና ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ አሳሰበ፡፡በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙርያ ወረዳ ሥር የሚገኙ ኤ…

ኢሰመኮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የተከሰተው ውጥረት እና ግጭት ከመባባሱ በፊት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ አሳሰበ፡፡

በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙርያ ወረዳ ሥር የሚገኙ ኤልጎ፣ ወዘቃ፣ ደምብሌ እና ጫሞ 01 የተባሉ አራት ቀበሌዎች ከጋሞ ዞን በመውጣት ልዩ ወረዳ ሆነው ለመደራጀት በተለያየ ጊዜ ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩ ሲሆን፤ በተለይ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ውዝግቡ እየተባባሰ እንደመጣ ተገልጿል፡፡

ከግጭቶቹ ጋር በተያያዘ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ አስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ በአፋጣኝ ማቅረብን ጨምሮ፣ ተፈናቃዮች እና ነዋሪዎች ወደ ዘላቂ ሰላም የሚመለሱበት ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ ይገባል ነዉ ያለዉ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሸን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በጋሞ ዞን፣ አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ በተለይም ከአካባቢ አስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ጋር በተያያዘ ከነዋሪዎች ጥያቄ መነሳት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የሚመለከታቸዉን አካላት በማነጋገር የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ውትወታ ሲያደርግ መቆየቱንም ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ በአካባቢው እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገሩ፤ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድን ተከትለው እንዲፈቱ ለአካባቢው የመንግሥት አስተዳደር፣ ለአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ምክረ ሐሳብ በማቅረብ ሁኔታው ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ ብሏል፡፡

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በተለያዩ መድረኮች እና ወቅቶች በሚያነሱት በዚህ የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ ምክንያት ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙባቸዉ ገልጸዋል፡፡

በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት ለሁለቱም ምክር ቤቶች የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲን በመምረጣቸው ምክንያትም የጋሞ ዞን አስተዳደር በተለያየ መንገድ ስልታዊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጽሞብናል በማለት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ የመዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች የአካባቢ ምርጫ ተካሂዶ አካባቢውን ለማስተዳደር ሕግን በተከተለ መንገድ ምርጫውን በማሸነፍ ሥልጣን ሳይረከቡ መንግሥት ቀበሌዎቹን ማስተዳደር የለበትም በሚል ምክንያት በአካባቢው የመንግሥት መዋቅር እንዲፈርስና አካባቢው እንዳይረጋጋ እያደረጉ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የአስተዳደር መዋቅር ጥያቄ አቅራቢዎች እና በዞኑ አስተዳደር መካከል በሚፈጠሩ ተደጋጋሚ አለመግባባቶች ምክንያት በአካባቢው ነዋሪዎችና በጸጥታ ኃይል አባላት ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት፣ እንዲሁም የዘፈቀደ እስር እና የንብረት ውድመት እያደረሱ መሆኑን ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ገልጾ፤ ምርመራው ሲጠናቀቅ ሙሉ ሪፖርቱ ይፋ እንደሚያደርግ አስታዉቋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/@onelovebroadcast/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Website https://ethiofm107.com/

Telegram (https://t.me/ethiofm107dot8

Source: Link to the Post

Leave a Reply