ኢሰመኮ የጋምቤላ ጽሕፈት ቤት ሰራተኞቹ በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው አስታወቀ

ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ትናንት መስከረም 25/2015 በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመግባት የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን መፈጸማቸውንና በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ማድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ግለሰቦቹ በከተማዋ የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ሥራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይ ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰው ድርጅቶቹ “ከከተማው ለቅቀው እንዲወጡ” ማስፈራራታቸውንም ኢሰመኮ ዛሬ መስከረም 26/2015 ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው በጋምቤላ ከተማ በብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በአፋጣኝ ሊያስቆሙ ይገባል ብሏል፡፡ኢሰመኮ ሰኔ 7/2014 በጋምቤላ ከተማ ላይ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖቹ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት መስከረም 18/2015 ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ኦሰመኮ ያወጣውን የምርመራ ሪፖርት የክልሉ መንግሥት የማይቀበለው መሆኑን በከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ኢሰመኮ ያወጣው ሪፖርት ከሰኔ 7 እስከ 9/2014 በክልሉ ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር፡፡

ሆኖም የሪፖርቱን ይፋ መደረግ ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች እና መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ፣ አነሳሽ እና ዛቻ ያዘሉ መረጃዎች ሲሰራጩ፤ እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልዕክቶች ሲዘዋወሩ መቆየታቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል በማመን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ መቆየቱን ገልጿል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥት የተቋቋመ ፌዴራል የብሔራዊ ሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑንና የኮሚሽኑ ሠራተኞችም በአዋጅ የልዩ መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው በመሆኑ፣ “ይህንን አይነት በብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል” ብለዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም ኮሚሽኑ የክትትል እና የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት ጠቁመዋል፡፡

ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9/2014 የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ሟቾች የተቀበሩበትን ቦታ ለማወቅ እና ፍትሕ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው የኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቦች በአፋጣኝ እንዲተገበሩ ኮሚሽነሩ በድጋሚ አሳስበዋል፡፡

The post ኢሰመኮ የጋምቤላ ጽሕፈት ቤት ሰራተኞቹ በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው አስታወቀ first appeared on Addis Maleda.

Source: Link to the Post

Leave a Reply