የኢትዮጵያ ስደተኞች በሳውድ አረቢያና የመን ድንበር ላይ በጸጥታ ሃይሎች በስናይፐርና ሞርታር የጀምላ ግድያ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሚክስድ ሞኒተሪንግ ሴንተር ገለጸ፡፡
በስደተኞች ጥናትና ክትትል ላይ የሚሰራው ሚክስድ ሞኒተሪንግ ሴንተር የተሰኘው አለምቀፋዊ ድርጅት ለሚድል ኢስት አይ እንደገለጸው፤ የኢትዮጵያውያን የጀምላ ግድያና ጾታዊ ጥቃት እንደቀጠለ ነው፡፡
የድርጅቱ ዳይሬክተር ብራም ፍሮስ የኢትዮጵያ ስደተኞችን በሳውድ አረቢያና የመን ድንበር ላይ በስናይፐርና ሞርታር የጦር መሳሪያ የጀምላ ግድያ እንዲሁም የጅምላ እስር እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጀምላ ጭፍጨፋው ከታህሳሰ 2014 ጀመሮ እስከ አሁን ደረስ የቀጠለ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ የጅምላ ግድያው አልጃሁ እና ሳዳህ በተባሉ አካባቢዎች እንዲሁም በሳውድ አረቢያ ጅዛን ግዛት እየተፈጸመ መሆኑን አመላክቷል፡፡
ከታህሳስ 23 እስከ ሚያዚያ 22//2014 ደረስ ብቻ ከ430 በላይ ሰዎች መሞታቸውንና ከ650 በላይ መቁሰላቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ በተለይ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የሳውዲ የመን ድንበር አደገኛ ሆኗል ሲል ገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት አካባቢው በአስከሬኖች መሙላቱንና ከባድ የሆነ ሽታ እንዳለውም ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያን ሰደተኞች በሳውዲ አረቢያ እና በተለያዩ የወጭ አገራት እስር ቤቶች እና በዱር በበረሃ በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ እንደሚገኙ እንዲሁም ለሞት እየተዳረጉ መሆኑን በተደጋጋሚ እየተነገረ ቢሆንም፤ እስካሁን መፍትሔ ማግኘት ሳይቻል በመቅረቱ ችግሩ ሳይቀረፍ መቀረቱ ተመላክቷል፡፡
ሳውዲ እና የመን የምስራቅ አፍሪካ የማዕከላዊ ምስራቅ መተላለፊያ መስመር ቢሆኑም፤ ኢትዮጵያውያን በጀምላ እየተገደሉ መሆኑን ጠቁሞ የአለም ማህበረሰብ ሊደርስለት እንደሚገባና ሁኔታውን አጣርቶ መፍትሄ እንዲያመጣ ሚክስድ ሞኒተሪንግ ሴንተር ጥሪ አቅርቧል።
Source: Link to the Post