ኢትዮጵያውያን ሃገራቸውን እንዲታደጉ እናት ፓርቲ ጥሪ አቀረበ

 “ለኢትዮጵያውያን የቀረበው ወቅታዊ ምርጫ ነፃነት ወይም ሞት ነው”
                                     አለማየሁ አንበሴ

                ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለክብራቸው ለነፃታቸውና ለሃገራቸው አንድነት መጠበቅ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው አሸባሪውና ሃገር አፍራሹ ህወኃት ላይ በሚወሰደው እርምጃ ግንባር ቀደም ተካፋይና የታሪክ ባለቤት እንዲሆኑ እናት ፓርቲ ጥሪ አቀረበ፡፡
እናት ፓርቲ “በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ፍላጎትን በሃይል እጭናለሁ ብሎ ማሰብ እብደትም እብሪትም ነው፤ ህዝብም በተባበረ ክንድ ይመክተዋል” በሚል ርዕስ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የጦር ክተት ጥሪ አቅርቧል፡፡
“ሃገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ተፈትና ይሆናል እንጂ ወድቃ ተሸንፋ አታውቅም” ያለው የፓርቲው መግለጫ እንዲያውም በመከራው  ፅናት እንደ እንቁ አብርታና ዕልፍ ጀግኖቿን ወልዳ ለራሷም ለአለምም መኩሪያ ሆናለች፤አሁንም ሃገር ለማፍረስ የተነሱ ሃይሎችን የኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ ምላሽ ይሰጣቸዋል” ብሏል፡፡
ህወኃት ከፍጥረቱ ጀምሮ ጥፋት የተጣባውና ባለፉት 27 ዓመታት በምኒሊክ ቤተ መንግስት ተቀምጦ እንደ ቅኝ ገዥ ሲኖር የነበረ መሆኑን ያመለከተው እናት ፓርቲ፤ አሁንም እኔ ያልገዛኋት ሃር ለማንም አትሆንም ትበተን በሚል ቅዠት ህዝብን ለዳግም ባርነት፣ ስደት ማኮላሸትና ግድያ ቋምጦ እየተፍጨረጨረ ይገኛል ብሏል፡፡
“ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ወቅታዊ ምርጫው ነፃነት ወይም ሞት ነው “ያለው ፓርቲ መልሱ ግን ነፃነት መሆኑ ላይ ምንም ጥርጥር የለውም፤ሆኖም ነፃነት በችሮታ አይመጣም፤ ለነፃነት በመሞት እንጂ፤ ስለሆነም መላው ኢትዮጵያውያን ፊታችን በዚህ እኩይ ቡድን ላይ እንድናዞር፣የተባበረ ክንዳችንንም እንድናሳርፍና የአባቶቻችንን የነፃነት ገድል ዳግም እንድንፅፍ ጥሪያችንን  እናቀርባለን” ብሏል  በመግለጫው፡፡
የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ሁሉ ሃገርን የመታደግ ተግባርን እንዲቀላቀሉና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ፣ ለፌደራል መንግስቱ ባስተላለፈው ለጦርነቱ ግልፅ ግብ ከማስቀመጥ ጀምሮ ትኩረት ከሚበትኑ ጉዳዮች በመራቅና አካሄዱን  ደግሞ በእውቀት በጥበብና ተጠያቂነት ባለበት መልኩ እንዲመራ፣ መረጃዎች ለህዝብ በመደበኛነት እንዲቀርቡ፣የቀድሞ የጦር ጠበብቶች ሙያዊ እገዛ የሚያደርጉበት መንገድ እንዲመቻች የጠየቀ ሲሆን በተጨማሪም የአፋርና የአማራ ክልሎች በጀታቸውን በሙሉ ለጦርነቱ ማዋላቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የፌደራል መንግስቱ የባጀት ሽግሽግ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው፣ ለዚህ ሀገር የማዳን ጥሪ እንዲሰለፉ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply