ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌቷን የሚያቋርጣት ምንም ኃይል የለም ሲሉ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ፡፡

የህዳሴ ግድብ ድርድሩም በሦስትዮሽ እንደሚቀጥል ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ የሦስትዮሽ ድርድሩን በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት ሚኒስትሩ ድርድሩ በሦስቱ ሀገራት ይቀጥላል፤ የማያግባቡ እና የማያስማሙ ጉዳዮች እልባት እየተሰጣቸው ይሄዳል ብለዋል፡፡

የግድቡን ግንባታ ለማስጀመር 78 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የተገለፀ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ለግንባታው 121 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ የገለፁት ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ናቸው፡፡

በአሁኑ ሰዓት የግንባታው አጠቃላይ ሂደት 79 በመቶ መጠናቀቁን ኢንጂነር ክፍሌ ገልፀው ቀሪው 21 በመቶውን በቀጣይ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሲቪል ስራውም 91 ነጥብ 2 በመቶ የኮርቻ ግድብ 99 በመቶ፣ የጐርፍ ማፍሰሻ 97 በመቶ፣ የኃይል ማመንጫ 54 በመቶ መድረሱ ተገልጿል፡፡ግድቡን በቶሎ አጠናቆ ወደ ሥራ ለማስገባት ኢትዮጵያ በትኩረት እየሰራች መሆኗን ኢንጂነር ክፍሌ ገልፀዋል፡፡

ቀን 08/07/2013

አሐዱ ራድዮ 94.3

Source: Link to the Post

Leave a Reply