ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ኤክስፖርት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ

ሐሙስ መስከረም 5 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቡና ኤክስፖርት 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።

ባለስልጣኑ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን የዘንድሮ ዓመት የኢትዮጵያ የቡና ቀንን ‹‹ቡናችን ለአብሮነታችን እና ለብልፅግናችን›› በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ይገኛል፡፡የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዑመር ሁሴን በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደተናገሩት፤ የቡና ዘርፉ በግብርና ዘረፍ ካሉት የውጭ ምንዛሪ ግኝት የጎላ ድርሻ የነበረው ሲሆን፤ በዘንድሮው ዓመት ከሌሎች ዓመታት በተለየ መልኩ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም አስተዋጾ ለነበራቸው ባለድረሻ አካላት የእውቅናና ሽልማት የሚሰጥበት መድረክ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም በመድረኩ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዳይሬክተር በሆኑት ዶ/ር አዱኛ ደበላ ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡ ከቀረቡት አንኳር ጉዳዮች መካከል ኢትዮጵያ እንደ አገር የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከቡና ዘርፍ ጋር ተጠቃሚ በመሆናቸው ቡና ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ወርቅ ነው ብለዋል፡፡

የቡና ምርትና ኤክስፖርት ወደ 300 ሺህ ኩንታል እያደገና 843 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ እያመጣ እንደሚገኝም በመነሻ ጽሁፉ ላይ ቀርቧል፡፡

በመጨረሻም በግብርና ሚኒስትሩ ዑመር ሁሴን የሚመራ የውይይት መድረክ የተካሄደ ሲሆን፤ በውይይቱ ላይም በቡና ምርትና ምርታማነት በተፈለገው መልኩ እንዲያድግ ከባለሃብቱ ምን ይጠበቃል? የኤክስፖርት መጠን በአለም ገበያ ለማሳደግና አገራችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአቅራቢው ምን መሰራት ይኖርበታል? በቡና ላይ መንግስታዊ ያልሆነ ድረጅት ተመራማሪ ሚና እና እንደ አገር የአርቢካ ቡና በአየር ንብረት ለውጥ በመጠቃት የሚያጋጥመውን ችግር ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው የሚሉ ጉዳዮች ቀርበው ውይይትና ማብራሪያ እንደተደረገባቸው አዲስ ማለዳ በግብርና ሚኒስቴር ያገኘችው መረጃ አመላክቷል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply