ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከኢንሸስትመንት ዘርፍ ለማግኘት እየሰራች መሆኑ ተገለጻ

ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከኢንሸስትመንት ዘርፍ ለማግኘት እየሰራች መሆኑ ተገለጻ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከኢንሸስትመንት ዘርፍ ለማግኘት እየሰራች መሆኑን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በኢንቨሰትመንት ህጉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን አስመልክቶ ለአሜሪካና ለካናዳ ኢንቨስተሮች ገለጻ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳንኤል ተሬሳ እንደገለጹት፤ አገሪቷ ካካሄደችው የኢኮኖሚ ሪፎርሞች መካከል አንዱ የኢንሸስትመንት ህጉን ማሻሻል ነው።

ከዚህ በፊት በዘርፉ የነበረው የህግ ማዕቀፍ የውጭ ኢንሸስተሮች በስፋት እንዳይሳተፉ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን በተደረገው ሪፎርም በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አብራርተዋል።

በበጀት አመቱም 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከዘርፉ ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ በዘርፉ እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመቋቋም እቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ህጉ ላይ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የሆኑ ስራዎች ውስን እንደነበሩ አስታውሰው፤ መንግስት እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ይህን የሚለውጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በበኩላቸው የተደረጉት ማሻሻያዎች አገሪቷ ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረች መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካን የንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኤርሚያስ እሸቱ እንደሚሉት፤ “ከዚህ በፊት የነበሩት ህጎች ለውጭ ባለሃብቶች አስቻይ ሁኔታዎች ያልፈጠሩ ነበሩ” ብለዋል።

የአሜሪካው ቫርዳንት ኮንሰልቲንግ ማኔጀር ወይዘሮ ትዕግስት ገረመው በበኩላቸው በመንግስት በኩል እየተደረጉ ያሉት ማሻሻያዎች መልካም የሚባሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ሆኖም ከመሬት አስተዳደር፣ ከግብር እና ከውጭ ምንዛሬ ጋር የነበሩትን ችግሮች ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አሁንም ወሳኝ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የፈጠራቸውን ምቹ ሁኔታዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር መስራት አለበት” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

The post ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከኢንሸስትመንት ዘርፍ ለማግኘት እየሰራች መሆኑ ተገለጻ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply