ኢትዮጵያ በቻይና ገበያ ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑ ተገለጸ

አርብ ሐምሌ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ በቻይና የኦንላይን ግብይት መድረኮች ላይ የምታቀርባቸውን የምርት አይነቶች በመጨመር በገበያው ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዳዋኖ ከድር ገለጹ፡፡

ሚሲዮኑ ከሐምሌ 27 እስከ ዛሬ የጄጂያንግ ክፍለ አገር ርዕሰ መዲና በሆነችው፤ የሀንጆ ከተማ በተካሄደው 9ኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ግብይት አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፏል።

አምባሳደር ዳዋኖ ከድር በአውደ ርዕዩ የመክፍቻ መርሐ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በቻይና የበይነ መረብ ግብይት መድረኮች ላይ የምታቀርባቸውን የምርት አይነቶች በመጨመር በገበያው ያላትን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩና ልምድ ያካበቱ የቻይና ኩባንያዎች የኢትዮጵያ የውጭ ሽያጭ ምርቶች በቻይና የበይነ መረብ መገበያያ መድረኮች ላይ በስፋት እንዲገቡ ለማድረግ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በአውደ ርዕዩ ቡናን ጨምሮ ለውጭ ሽያጭ የሚቀርቡ የተለያዩ የኢትዮጵያ ምርቶች ለእይታ ቀርበው በተሳታፊዎች መጎብኘታቸም ታውቋል።

ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም አምባሳደር ዳዋኖ ከሀንጆ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ ከጄጂያንግ ውጭ ጉዳይ ቢሮና ከጂጂያንግ- አፍሪካ የንግድ አገልግሎት ማዕከል ሃላፊዎች እንዲሁም ከአሊባባ ኩባንያ ተወካዮች ጋር በበይነ መረብ ንግዱ ዘርፍ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት መካሄዱን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply