ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የምታስከብርበት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች – አምባሳደር ረታ ዓለሙ

ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የምታስከብርበት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች – አምባሳደር ረታ ዓለሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የምታስከብርበት ወሳኝ ወቅት ላይ መሆኗን በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ረታ ዓለሙ ተናገሩ፡፡
 
አምባሳደሩ ይህንን ያሉት በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ “በአባይ ፍትሃዊ የውሃ ድርሻ የማስከበር ጥያቄ” በሚል ርዕስ የዌቢናር ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡
 
አምባሳደሩ በናይል ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት አካባቢ ሰላምን፣ መረጋጋትን እና ብልጽግናን ሊያመጣ የሚችለው ብቸኛው እና የተሻለው መንገድ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አካሄድ መከተል ሲቻል ብቻ ነው ብለዋል።
 
በኢትዮጵያ የሚደረገው ጥረትም ተያያዥነት ባላቸው ዓለም አቀፍ የሕግ መርሆዎች ላይ የተመሠረተ እውነተኛ የትብብር ጥሪ መሆኑንም አውስተዋል።
 
በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ በርካታ መጽሐፍትን የጻፉት ታዋቂው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ሀጋይ ኤርሊኽ በበኩላቸው፥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የናይል ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት መሆኑን ተናግረዋል።
 
በቅርቡ ከአስዋን እስከ ሕዳሴ ግድብ የሚል መጽሐፍ ያሳተሙት ምሁሩ በግብጽ የሚገኘው የአስዋን ግድብ 15 በመቶ የሚሆነው ውሃ በትነት እንደሚባክን በምሳሌነት አቅርበው ይህን ለመለወጥ በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸዋል።
 
የናይል ወንዝ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ልጆች የጋራ ሀብት መሆኑን ጠቅሰው ውሃ ለማጠራቀም ትክክለኛው የውሃው ማስቀመጫ ቦታ ግን አሁን ታላቁ ህዳሴ ግድብ የተቀመጠበት መሆኑን፣ ይህም በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን መጀመሪያ በእንግሊዞች ቀጥሎም በአሜሪካኖች በተደረጉ ጥናቶች መረጋገጡንም አንስተዋል።
 
አያይዘውም ግድቡ በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የልማት አብዮት ማሳያ መሆኑን በመጥቀስም ለተፋሰሱ ሃገራት የግድቡ ፋይዳ ሊካድ የማይችል እና ሊቀበሉት የሚገባ ሀቅ መሆኑንም አስረድተዋል።
 
ግብጻውያን ይህን አዲስ እውነታ መቀበል እና አመለካከታቸውን ማስተካከል አለባቸው በማለትም አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
ኢትዮጵያ እና ግብፅ ያለ አንዳች ጣልቃ ገብነት እና ያለ ኃያላን ሀገራት የአዛዥ አቀራረብ ልዩነቶቻቸውን በውይይት መፍታት አለባቸውም ነው ያሉት፤ ይህን ማድረግ እንደሚችሉ በመጥቀስ።
የታሪክ ምሁር ዶክተር ኦፊር ደግሞ በአባይ ወንዝ የውሃ እጥረት የሚፈጠሩ ውዝግቦችና አሁን ያሉትን ሥጋቶች ለመቅረፍ ትብብር መፍትሄ መሆኑን ያነሳሉ፡፡
 
ቴክኖሎጂን በመጠቀም በአካባቢው ባለው የፈጠራ ጥበብ የውሃ እጥረትን፣ ድርቅን እና የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከቀይ ባህር ውሃን በመውሰድ አጣርቶ መጠቀም ለሁሉም መፍትሄ ሊሆን እንደሚችልም ይገልጻሉ፡፡
 
 
 
በስላባት ማናዬ

The post ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የምታስከብርበት ወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች – አምባሳደር ረታ ዓለሙ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply