ኢትዮጵያ በክልላዊ ጫና ዉስጥ በመሆኗ የሶማሌላንድን እዉቅና ልትሰርዝ ትችላለች ተባለ፡፡

በስምምነቱ የተነሳ የተፈጠረዉን ቀጣናዊ ዉጥረት ለማርገብ አለም አቀፍ ግፊት እየተደረገ ባለበት በዚህ ሰዓት ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ መንግስት እውቅና ለመስጠት የያዘችዉን እቅድ ለመሰረዝ እያሰበች ነዉ መባሉን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰዎች ነግረዉኛል ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡

የባህር በር የሌላት ኢትዮጵያ ጥር ወር ከሶማሌላንድ ጋር የመጀመሪያ ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን፤ይህም ከፊል ራስ ገዝ ለሆነችዉ የሶማሊያ ክልል ሉዓላዊነት እውቅና የሰጠች የመጀመሪያዋ ሀገር እንድትሆን በምላሹም ለ50 አመታት የኤደን ባህረ ሰላጤን እንድትጠቀም የሚያደርግ ነበር፡፡

ስምምነቱ በጎረቤት ሀገራት ግርግርን የፈጠረ ሲሆን፤ሶማሊያ የግዛት አንድነቴን እጠብቃለሁ ስትል ግብፅ እና ሌሎች ሀገራትም ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰባቸዉ ይታወሳል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና የኬንያው አቻቸው ዊሊያም ሩቶ ባለፈው ሳምንት በናይሮቢ በጉዳዩ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሶማሊያ ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት በስምምነቱ ዉስጥ ካሉ በጣም አወዛጋቢ ጉዳዮች ለመውጣት ፈቃደኛ መሆናቸውን ስለመግለጻቸዉ ጉዳዩን ይፋ ለማድረግ ስልጣን የለንም ያሉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሰዎች ነግረዉኛል ብሏል ብሉምበርግ፡፡

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ሀገሪቱ ለሶማሌላንድ ያላትን እውቅና ለማቋረጥ ፍቃደኛ ልትሆን እንደምትችል ለውጭ ባለስልጣናት በግል ነግረዋቸዋል ሲሉ የአዲስ አበባን አቋም በተመለከተ የተነገራቸው አምስት የውጭ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ሩቶ ጉዳዩን ያነሱት ከአብይ ጋር በተመሳሳይ ጊዜ ኬንያን እየጎበኙ ከሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ጋር ባደረጉት ውይይት ነው።

ሩቶ በጥር ወር ለብሉምበርግ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩትም መንግስታቸዉ  ኢትዮጵያ ከወደብ ፍላጎት በላይ ሌሎች አማራጮችን እንድታስብ ለማድረግ እየሞከረ ነው ያሉ ሲሆን፤እነዚህ አማራጮች ምን እንደሆኑ ግን በግልጽ አላስቀመጡም።

ኢትዮጵያ እስካሁን ከሶማሌላንድ ጋር ከተደረሰው ስምምነት በይፋ ያልወጣች ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም አሁንም ወደ ባህር ዳርቻው በቀጥታ የመድረስ አላማቸውን ለማሳካት ፍላጎት እንዳላቸው በመነገር ላይ ይገኛል፡፡

ሶማሊያ ህገወጥ ነው ያለችው እና የግዛት መካለልን ይወክላል ያለችውን ይህን ስምምነት ቀድሞውንም ተለዋዋጭ በሆነው ክልል ውስጥ ግጭት ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ጎረቤት ሀገራት እና አንዳንድ የኢትዮጵያ ትልልቅ ለጋሾች ስጋታቸውን ከዚህ በፊት መግለጻቸዉም የሚታወስ ነዉ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ ፣ ባለፈው ወር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የባህር ላይ መዳረሻ የምትፈልግ ከሆነ በሞቃዲሾ ከሚገኙ የፌደራል ባለስልጣናት ጋር እንጂ በሶማሌላንድ ካሉ ባለስልጣናት ጋር መነጋገር የለባትም ብለዉ ነበር።

አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስምምነቱ እስላማዊው ታጣቂ ቡድን ‹‹አልሸባብ›› ሁኔታውን ለመመልመያው እንዲጠቀምበት ሊፈቅድለት ይችላል ሲሉም ስጋታቸዉን ገልጸዋል፡፡

ሞሊ ፊ “ክልሉ ከዚህ የበለጠ ግጭትን ሊያስተናግድ አይችልም” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ፣ የኬንያ እና የሶማሊያ መንግስት ቃል አቀባዮች የሶማሊላንድ ስምምነት ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

የሶማሊላንድ መንግስት በጥር ወር ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት “ወደ ቀጣናዊ መረጋጋት እና ብልጽግና የሚያስኬደን አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ያሳያል” ሲል ባለፈው ማክሰኞ ባወጣዉ መግለጫ ገልጿል።

ሶማሌላንድ በ1991 የእርስ በርስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ከሶማሊያ ነፃነቷን አውጃለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም የውጭ የገንዘብ ድጋፍ እና እርዳታ ለማግኘት የሚያስችላትን ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት ግፊት እያደረገች ቆይታለች፡፡ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገው ስምምነት የረጅም ጊዜ አላማዋን ለማሳካት ትንሽ እርምጃ ይሆናታል ተብሏል፡፡(ብሉምበርግ)

በእስከዳር ግርማ

የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply