ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆና ተመረጠች

ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆና ተመረጠች። ምርጫው የተከናወነው በጄኔቫ በመካሄድ ላይ በሚገኘው እና ዛሬ በሚጠናቀቀው 75ኛው የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው። 

የዓለም ጤና ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ በየአገሮቻቸው የተወከሉ 34 የጤና ባለሙያዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው። ሥራ አስፈጻሚ ቦርዱ አባል ሆነው የሚመረጡ አገራት ለሶስት አመታት ያገለግላሉ። ቦርዱ በዋናነት የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች እና ፖሊሲዎች የማስፈጸም፣ ስራውንም ለማመቻቸት የማማከር ኃላፊነት አለበት። 

በጄኔቫ ለሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማህሌት ኃይሉ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆነው ከተመረጡ 12 ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን በትዊተር ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል። በምርጫው ውጤት መሰረት፤ የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅት የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆነው ይሰራሉ።

ከባለፈው እሁድ ግንቦት 14 ጀምሮ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያዊው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም ድርጅቱን እየመሩ እንዲቆዩ በድጋሚ ተመርጠዋል። ዶ/ር ቴድሮስ ለመሪነት የቀረቡት ያለምንም ተቃናቃኝ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

The post ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆና ተመረጠች appeared first on Ethiopia Insider.

Source: Link to the Post

Leave a Reply