You are currently viewing “ኢትዮጵያ ትናንት ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለው ያሻገሯት ሀገር ናት፤ ዛሬም ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለን እናስቀጥላታለን” ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቴዎስ  ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ)…

“ኢትዮጵያ ትናንት ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለው ያሻገሯት ሀገር ናት፤ ዛሬም ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለን እናስቀጥላታለን” ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቴዎስ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ)…

“ኢትዮጵያ ትናንት ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለው ያሻገሯት ሀገር ናት፤ ዛሬም ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለን እናስቀጥላታለን” ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቴዎስ ጥቅምት 19/2014 ዓ.ም (አሻራ ሚዲያ) ኢትዮጵያዊ ሁሉ የኢትዮጵያ እዳ አለበት፡፡ ዓለም ከተፈጠረ ዘመን ከተቆጠረ ጀምሮ ገናና እና አያሌ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ኑባሬዋ ያለዋጋ የተገኘ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል እልፍ ሕይዎት አልፎላታል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሀገረ መንግሥቷ በጽኑ ዓለት ላይ እንዲጸና አጥንት ተከስክሶ ደም ፈሶ ዋጋ ተከፍሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ነፃነት እና አልደፈርም ባይነት በችሮታ የታደለ ሳይሆን በችሎታ የተገኘ ነበር፡፡ ስለኢትዮጵያ ክብር ሲባል ነገሥታት ከዙፋናቸው ወርደው በአውደ ውጊያዎች ላይ መተኪያ የሌላትን ሕይዎታቸውን ሰጥተዋታል፡፡ ስለ…ኢትዮጵያ ነፃነት ሲባል ቅዱሳን ጳጳሳት በአንድ እጃቸው መስቀል በሌላ እጃቸው ጦር ይዘው ተፋልመዋል፡፡ ስለኢትዮጵያ መቀጠል ሲባል ደረሶች ከቁርዓን ሼኮች ከመስጂድ ተለይተው አንገታቸውን ስለሀገራቸው አሳልፈዋል፡፡ ስለኢትዮጵያ ሲሉ እልፎች በየዱሩ፣ በየገደሉ እና በየበርሃው አልፈዋል፡፡ በየዘመኑ ብቅ የሚሉ የትውልድ ሀረጎች ሁሉ የኢትዮጵያ እዳ አለባቸው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለኢትዮጵያ ሲል ራሱን ሊያሳልፍ የታሪክ እዳ አለበት፡፡ ወታደር ስለኢትዮጵያ ነፃነት እና ክብር ከሁሉ ቀድሞ ሕይወቱን ጭምር የሚሰጥ የሀገር ዘብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ደግሞ ይህንን የዘመናት ገናና ስምና ዝና ከነክብሩ የማቆየት ኅላፊነት በታሪክ አጋጣሚ ትከሻቸው ላይ ወድቋል፡፡ ስለኢትዮጵያ ክብር ሲሉ ቀን ከሌሊት ቆመው ያድራሉ፡፡ ስለኢትዮጵያውያን ሰላም ሲሉ ዳሯን ከበው ይኖራሉ፡፡ ይህ ትናንት የነበረ፣ ዛሬ ያለ እና ነገም የሚኖር የኢትዮጵያዊ ወታደር ልዩ ስብዕና እና ቃል ኪዳን ነው፡፡ ዛሬም እንደትናንቱ ታሪክ፣ ሀገር እና ሕዝብ የሰጡትን ሙያዊ ኅላፊነት እስከ መጨረሻው ሲወጣ እና ለሌሎች አርዓያ ሲሆን ያየነውን አንድ ወታደር እና ኢትዮጵያዊ ፍቅሩን ለአብነት እንይ፡፡ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቴዎስ በ18 ዓመቱ ማለትም 2000 ዓ.ም ላይ ይህንን ታላቅ ዝናና እና ታሪክ ያለውን የውትድርና ሙያ እንደተቀላቀለ ይናገራል፡፡ በ14 ዓመታት የውትድርና ሙያ ቆይታው ከተዋጊነት እስከ ቡድን መሳሪያ ተኳሽነት፤ ከሐኪምነት እስከ ጋንታ መሪነት እና አዋጊነት ድረስ ሀገሩን እና ሕዝቡን አገልግሏል፡፡ ስለሀገሩ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ቃላት ይቸግሩታል፡፡ የውስጡን መግለጽ ሲያዳግተው “ሀገር እኮ በቃል የምትገለጽ አይደለችም” ሲል ከጭንቁ ለመገላገል ይሞክራል፡፡ ሀገሩን ይወዳል፣ ሙያውን ያከብራል ለጓዶቹ እና ለሚመራቸው ወታደሮች ያለው ፍቅር ደግሞ የተለየ ነው፡፡ ጓደኞቹን ሲያይ በፍቅራቸው ከድካሙ ይበረታል፡፡ የእናት ጡት ነካሾች የሚወዳት ሀገሩን፣ እርሱን እና ጓዶቹን የበደሉትን አሁንም እረፍት መንሳታቸው ሁሌም ይገርመዋል፡፡ “እኛን እኮ መጥላት እና መውጋት ካለባቸው ሌሎቹ ነበሩ እንጂ እነርሱ በፍጹም መሆን አልነበረባቸውም” ሲል ይገረማል፡፡ “ከመጀመሪያው ስሕተታቸው መታረም አለመቻላቸው እና ይቅርታ አለመጠየቃቸው አንሶ ጦር ሰብቀው ወረራ መክፈታቸው ደግሞ በእርግጥስ የሰው ዘር ለዚያውም ኢትዮጵያውያን ናቸው?” ሲል ይጠይቃል፡፡ ቀድሞ ከነበረበት ወታደራዊ የሕክምና ሙያ ወደ ጋንታ መሪነት እና አዋጊነት የመጣው በራሱ ፍላጎት ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የያዘውን ኅላፊነት በእጅጉ ይፈልገው ነበር፡፡ ተዋግቶ እና አዋግቶ ሀገሩን አስከብሮ ጠላቶቹን ድል ማድረግ ይፈልግ ነበርና ነው፡፡ እንደፈለገው ሆኖለታል፡፡ በሕልውና ዘመቻው በተለያዩ ግንባሮች እየተዋጋ እና እያዋጋ ብዙ ጊዜ በድል ተመላልሷል፡፡ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ እና ጓዶቹ ከሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን አባላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው ጀግንነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን በሠራው ምሽግ ውስጥ የመጨረሻ ፍፃሜው እስኪሆን በጽናት እና በጀግንነት ተዋግተዋል፡፡ ተወግተውም ድል ከእነርሱ ጋር ሆናለች፡፡ በአውደ ውጊያ ቀናት በአንዱ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ጋንታ መሪ፤ ቡድኗ ደግሞ የመጀመሪያ ምሽግ ሰባሪ ሆነው ገብተዋል፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድን ወታደራዊ ገዥ መሬት እና አስተማማኝ ያለውን ምሽግ ቢይዝም ለእነ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ግን አስፈሪ አልነበረም፡፡ በውጊያው እነ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ የሽብርተኛው ትህነግ ወራሪ ቡድንን ከምሽግ ሳይወጣ መደምሰስ እና ተልዕኮአቸውን በብቃት ማጠናቀቅ እንዳለባቸው ተነጋግረው ነው የገቡት፡፡ እልህ አስጨራሽ ውጊያ፣ የሞት ሽረት ትግል እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የበላይነት በተጎናጸፈበት በዚያ አውደ ውጊያ መጨረሻ አካባቢ ጦርነቱን በብቃት የሚመራው ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ቆሰለ፡፡ ጓዶቹ ምሽጉን እንደሚሰብሩት እርግጠኞች ናቸው፡፡ የእርሱን ክፍተት የመሙላት ወታደራዊ አቅም እንዳላቸው እና የጠላት ጦር ተስፋ እንዳጣ አውቀዋል፡፡ በዚህ መካከል ነበር የመቁሰል አደጋ የደረሰበትን የቡድን መሪያቸውን ወደ ሕክምና እንዲሄድ የጠየቁት፡፡ ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ከሚመራቸው ጓዶቹ ባየው የራስ መተማመን ተደስቷል፡፡ ጉዳቱን በእራፊ ጨርቅ ጠቅልሎ ያንን ውጊያ በብቃት መምራቱንም ቀጥሏል፡፡ በዚህ መካከል ሁሉ የዚያች ቡድን ወታደሮች ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ወደ ሕክምና እንዲሄድ ቢጠይቁትም አንድ አስደንጋጭ ነገር በቁርጠኝነት ነገራቸው፡፡ “ይህ ውጊያ ነው፤ በትንሽ ስህተት እና በሰከንዶች ሽርፍራፊ የሚፈጠረው አይታወቅም፤ የከበደ ነገር ቢመጣ እንኳን የጠላትን ፈንጂ ተረግጨ እና አምክኘ እናንተ በእኔ አስከሬን ላይ ተረማምዳችሁ የጠላትን ምሽግ ትሰብራላችሁ እንጂ እናንተን በዚህ ትቼ ብሞት እንኳን ወደ ሕክምና አልሄድም” ሲል ቁርጡን ነገራቸው፡፡ ወታደሮቹ በሰሙት ነገር ተገርመዋል፡፡ ብርታቱ ብርታት፣ እልኩ እልክ፣ ጀብደኝነቱ ጀብድ እና ጽናቱ ጽናት የሆናቸው ጓዶቹ በማይታመን ፍጥነት የጠላትን ምሽግ ዶግ አመድ አድርገውት ገቡ፡፡ የጠላት ጦር ለወሬ ነጋሪ እንኳን ባልተመለሰበት በዚህ አውደ ውጊያ እነምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ተልዕኳቸውን በፍጹም ጀግንነት አጠናቀቁ፡፡ ከውጊው በኋላም ወደ ሕክምና እንዲሄድ የተጠየቀው ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ በአካባቢው ባሉ ሐኪሞች እየተረዳ ከግንባር ፈቀቅ አልልም ነው ያለው፡፡ “እኔ እኮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ወታደር ነኝ” የሚለው ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ “በዚህ ስዓት በተፈጠረ ትንሽ ቁስል ሰበብ የምወዳቸውን ጓደኞቼን ትቼ ለሕክምና የማርፍበት ጊዜው አይደለም” ብሏል፡፡ “ኢትዮጵያ ትናንት ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለው ያሻገሯት ሀገር ናት፤ ዛሬም ሚሊዮኖች ዋጋ ከፍለን እናስቀጥላታለን” የሚለው ምክትል መቶ አለቃ ኤርሚያስ ማቴዎስ “በዚህ መካከል መስዋእትነትን መክፈል ቢጠይቅ እንኳን ከፍየ ትናንት ኢትዮጵያ እንድትቀጥል መስዋእትነት ከከፈሉ ሚሊዮኖች መካከል በታሪክ መዝገብ ላይ መስፈርን እመርጣለሁ” ነው ያለን፡፡ ይህ ጀብደኛ ወታደር ኢትዮጵያ አረሟ ሊነቀል የቀረው ትንሽ ጊዜ ብቻ ነው ሲል ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ የቆመበትን ይህን መሰል ጊዜ እንዳላየ እና በተፈጠረው ሀገራዊ አንድነት ደስተኛ እንደሆነም ነግሮናል፡፡ ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻው እስኪጠናቀቅ ድጋፉን እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡ ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://www.facebook.com/asharamedia24 ቴሌግራም :- https://t.me/asharamedia24 ለፈጣንና አዳዲስ መረጃዎች የአይበገሬዎቹ ልሳን:- https://t.me/asharamedia24 Facebook :- https://www.facebook.com/asharamedia24 ዩትዩብ:- https://bit.ly/33XmKro

Source: Link to the Post

Leave a Reply