ኢትዮጵያ አለም ዓቀፍ የኮንስትራክሽን ንግድ ትርኢት ልታካሂድ ነው

ዕረቡ ሰኔ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጽያ የአለም ዓቀፍ የኮንስትራክሽን ንግድ ትርኢት አካል የሆነውን “The Big 5 Construction Ethiopia” ለመጀመሪያ ጊዜ ልታዘጋጅ ነው።

ንግድ ትርኢት ከግንቦት 10 እሰከ 12/2015 ድረስ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ የኹነቱ አዘጋጅ የሆኑት “ኢቴል ኢቨንትስ” እና “ዲ ኤም ጂ ኤቨንትስ” በዛሬው እለት በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በዚሁ መግለጫ እና የፓናል ውይይት ላይ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዮናሰ አያሌው እንዲሁም ሌሎች የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተውበታል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር ዘርፉ የደረሰበትን የኮንስትራክሽን እና የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን የሚያስተዋውቁ መሰል መድረኮች መዘጋጀታቸው መንግስት በዘርፉ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ለዘርፉ የ30 ዓመት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን ያነሱት ሚንስትሯ ይህም በአገራችን ያለውን የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ የሚያሳድግ፣ የግንባታ ችግሮችን የሚቀርፍና ለብዙ ግለሰቦች የሥራ እድልን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የንግድ ትርኢቱ በኢትዮጵያ ለ10 ተከታታይ ዓመታት በኮንስትራክሽን ዘርፍ መካሄድ የነበረውን “AddisBuuld” የተሰኘውን የንግድ ትርኢት የቢግ 5 አዘጋጆች በባለቤትነት ከተረከቡ በኅላ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ ተገልጿል።

በንግድ ትርኢት ዝግጅቱ ከ 100 በላይ አለም ዓቀፍ የኮንስትራክሽን ምርቶች፣ አገልግሎት ሰጪ እና የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እና አገር በቀል ቁልፍ ተቋማትን ይዞ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply