ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቷ 0.2 በመቶ ብቻ የሚሆነዉን ለጥናት እና ምርምር እንደምታዉል ተገለጸ፡፡የአፍሪካ ሃገራት ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርታቸው 1 በመቶ የሚሆነውን በምርምርና ስር…

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቷ 0.2 በመቶ ብቻ የሚሆነዉን ለጥናት እና ምርምር እንደምታዉል ተገለጸ፡፡

የአፍሪካ ሃገራት ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርታቸው 1 በመቶ የሚሆነውን በምርምርና ስርፀት ሥራዎች ላይ ለማዋል የተስማሙ ሲሆን ኢትዮጵያም ይህንኑ ስምምነት ፈርማለች።
ከዚህ አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ለጥናት እና ምርምር የምታውለው በጀት እጅግ አነስተኛ መሆኑን ነው የተነገረዉ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የሳይንስና ምርምር ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ሰለሞን ቢኖር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በስምምነቱ ላይ ከተቀመጠው ቁጥር ባነሰ መልኩ ከሃገራዊ ምርቷ 0.2 በመቶ ብቻ ነው ጥናትና ምርምር ላይ ማዋል የቻለችው፡፡

እ.ኤ.አ 2016 ላይ በተሠራው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቷ ለምርምርና ሥርፀት 5.05 ቢሊየን ብር መድባ እንደነበር ያሳያል።
ከዚህም ከ66 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ የተሸፈነው ከመንግሥት ካዝና እንደነበረም ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡

በኢትዮጵያ ያሉ የግል ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ለምርምርና ሥርፀት ያወጡት ወጪ ከአጠቃላይ ከአጠቃላይ ወጭዉ ድርሻቸው አንድ በመቶ ብቻ ሲሆን አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ምርምርና ስርፀትን የሚከታተል ባለሙያ እንኳን የላቸውም።

እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሃገራት ግን የምርምርና ስርፀት ሥራዎች 50 በመቶ አንዳንዴም ከዚያ በላይ የሚሆነውን ወጪ የሚሸፍኑት የግል ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች መሆናቸውን ነው ጥናቶች የሚያሳዩት፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሯቸው የምርምር ውጤቶች አብዛኛዎቹ ወደ መሠረታዊ ጥናት ያጋደሉ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ይህ ደግሞ የሕዝቡን ችግር ተረድቶ መፍትሔ ማምጣት የሚችል ዓይነት ጥናት ሳይሆን፤ እውቀትን ለማዳበርና የትምህርት ደረጃን ከፍ ለማደረግ የሚሠሩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሄኖክ ወ/ገብርኤል
መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply