ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመጥቀም በድንበሯ ውስጥ ማንኛውንም ነገር የመስራት መብት አላት – የእስራኤል የደህንነት ምክትል ሚኒስትር

ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመጥቀም በድንበሯ ውስጥ ማንኛውንም ነገር የመስራት መብት አላት – የእስራኤል የደህንነት ምክትል ሚኒስትር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእስራኤል የሀገር ውስጥ ምክትል ሚኒስትር ጋዲ ይቫርከን 3 ሺህ 500 ዓመታት የነፃነት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመጥቀም በድንበሯ ውስጥ ማንኛውንም ነገር የመስራት መብት አላት ሲሉ ገለፁ።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው ጋዲ ይቫርከን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት ላይ ደብዳቤ ፅፈዋል።
ምክትል ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው ትራምፕ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት ቁጣን መፍጠሩን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ እና ግብፅ ጥንታዊ ህዝቦችን የያዙ መውደቅና መነሳትን ያዩ ግዙፍ ሀገራት እንደነበሩ ያነሱት ምክትል ሚኒስትሩ አሁንም በኩራት እና በስኬት በጉርብትና የሚኖሩ ሀገራት ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለ3 ሺህ 500 ዓመታት ነጻነቷን ያስጠበቀች ብቸኛ ሀገር መሆኗን የሚገልፁት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፖለቲከኛ ነፃ ሀገር ዜጎቿን ለመጥቀም በድንበሯ ውስጥ ማንኛውንም ነገር የመስራት መብት አላት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የታላቁ የህዳሴ ግድብን እየገነባች የሚገኘው ያለ ኤሌክትሪክ ሀይል በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ በሚሊየኖች ለሚቆጠሩ ዜጎቿ የኤሌክትሪክ ሀይል ለማቅረብ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ምክትል ሚኒስትሩ ለዶናልድ ትራምፕ በፃፉት ደብዳቤ ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ሀይል ተጠቃሚ ለሆኑባት አሜሪካ ልመክር የምፈልገው በኤሌክትሪክ ሃይል ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ህመም መረዳት ከባድ መሆኑን ነው ብለዋል።
የህዳሴ ግድብን በራሳቸው ገንዘብ እና በጠንከራ ስራ እንዲሁም እንደቀደሙት ቅድመ አያቶቻቸው ለተፈጥሯዊ መብቶቻቸው የቆሙትን በአስቸጋሪ የግብርና ስራ የሚታዳደሩትን ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች አከብራቸዋለሁም ብለዋል በደብዳቤያቸው።
በማንኛውም የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መግባት ዓለም አቀፍ ህግን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት ዲፕሎማቲክ ስርዓትን መጣስ መሆኑን አንስተዋል።
ነገር ግን የግብፅ መንግስት ከህዝብ ጥቅም ጋር ተያይዞ የሚያነሳቸውን ሁኔታዎች እንደሚያከብሩ እና እንደሚረዱም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያም ሆነች ግብፅ የእስራኤል እና አሜሪካ ጠንካራ ወዳጆች መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ሚኒስትሩ አሜሪካ እንደ ነፃ ዓለም መሪነቷ እውነታን በመያዝ ሀገራቱን እንድታስማማ ጠይቀዋል።
በመሆኑም አሜሪካውያን ለራሳቸው ትክክለኛ እና የተከበረ መፍትሄ በሚፈልጉበት መንገድ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ለሚያካሂዱት ውይይት ድጋፍ እንዲያደርጉም ነው የጠየቁት።
ውጫዊ ጫና ቢኖርም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ኢትዮጵያውያን በከባዱ የሚፈልጉትን ብልፅግና ያረጋግጣል ሲሉም ተስፋቸውን ገልፀል።

The post ኢትዮጵያ ዜጎቿን ለመጥቀም በድንበሯ ውስጥ ማንኛውንም ነገር የመስራት መብት አላት – የእስራኤል የደህንነት ምክትል ሚኒስትር appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply