ኢትዮጵያ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር እየቀነሰች ነው፤ 5 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ ሲጋራ ያጨሳል

ኢትዮጵያ የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ በአፍሪካ ስኬታማ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ናት ተባለ።

ከትንባሆ ነጻ ህጻናት (Campaign for Tobacco free Kids) የተሰኘ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ኢትዮጵያ ያለባትን የትንባሆ አምራቾች እና ተጠቃሚዎች ግፊት ተቋቁማ ለውጥ አምጪ የትንባሆ ቁጥጥር አዋጆችን አጽድቃለች ሲል አድንቋል።

ተቋሙ የትምባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶችን እና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ ዘጋቢ ተንቀሳቃሽ ምስል እና ዳሰሳውን ይፋ አድርጎ ለአዲስ ማለዳ ልኳል።

የተቋሙ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬከተር ቢንቶው ካማራ እንደገለጹት የትንባሆ ቁጥጥሩ ውጤታማነት በመንግስታዊ ተቋማት በሕብረት መስራት እና አገራዊ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው።

ዘጋቢ ፊልሙ ‘ጌትፊልድ’ በተባለ ማኅበረሰባዊ ለውጥ ለማምጣት በሚል የተቋቋመ ኩባንያ ባለቤትነት የተዘጋጀ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ኃላፊዎች ጋር ቃለ ምልልስን ያካተተ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ ከ6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከአጫሾች በሚወጣ የትምባሆ ጭስ እንደሚቸገሩ ከዚህ በፊት የተደረገ ጥናት ያሳያል። እንደ ሀገር በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ 5 በመቶ ያህሉ ትምባሆ አጫሾች ሲሆኑ ኢትዮጵያ የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ እና የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅ ጠንካራ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቷ ተመልካቷል።

ትምባሆ መግዛት የሚፈቀደው እድሜያቸው ከ21 ዓመት በላይ ለሆኑ ብቻ ማድረግ፣ የመዝናኛ እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ትምባሆ ማጨስ መከልከል፣ ሰው በተሰበሰበባቸው ቦታው ትምባሆ ማጨስ እና ማስጨስ መታገድ አስገዳጅ ሕግ መደረጋቸው ዋነኛ እርምጃዎች መሆናቸውን ተቋሙ ገልጿል።

በተጨማሪም በትምባሆ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ግብር መጣሉ እና የትምባሆ ምርቶችን በብዙሃን መገናኛዎች ላይ ማስተዋወቅ መከልከሉም ኢትዮጵያ የትምባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ አግዘዋል ተብሏል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከትምባሆ አምራች ድርጅቶች የሚደርሱ ጫናዎችን በመቋቋም የሲጋራ አጫሾችን ቁጥር በመቀነስ ስኬታማ አገር እንድትሆን አስችሏል ሲል ከትንባሆ ነጻ ህጻናት ተቋም አስታውቋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply