
ኢትዮጵያ በኃይልና በወረራ ፍላጎቷን ማሳካት እንደማትሻና በጎረቤት አገራት ላይ ወረራ የመፈጸም ፍላጎት እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ ። “አገሪቱ ቃታ በመሳብ በሀይልና በወረራ ማሳካት የምትሻው አንዳችም ነገር እንደሌላትም ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከበረው “116ኛ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን” በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ኢትዮጵያ ቃታ በመሳብ በኀይልና በወረራ ማሳካት የምትሻው አንዳችም ነገር የለም፤ ይልቁንም በንግግርና በድርድር የጋራ ጥቅሞችንና ፍላጎቶችን ለማሟላት ቁርጠኛ ነን፤” ብለዋል።
የዘንድሮው የመከላከያ ሠራዊት ቀኑ “በተፈተነ ጊዜ ሁሉ የሚፀና የድል ሠራዊት” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶችና የሠራዊቱን አቅምና ብቃት የሚያሳዩ ደማቅ ዝግጅች በቀረቡበት ሥነ-ስርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ስታነሳ ወረራ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ይደመጣል። ነገር ግን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በዚሁ በተከበረ ቀን መግለጽ የምፈልገው ኢትዮጵያ በሃይልና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር አለመኖሩን ነው” ብለዋል።
በሀይል ፍላጎቶቻችንን ለማሳካት ወንድሞቻችን ላይ ቃታ የምንሰነዝር እንዳልሆን በአጽንኦት ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ እድገት፣ ለጋራ ብልጽግና ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርጉ ጉዳዮች ከወንድሞቻችን ጋር ተወያይተን የጋራ ጥቅም ለማስከበር እንጥራለን ብለዋል። “የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ሰላም ከማስከበር፣ ሰላም ከመጠበቅና የሀገር ብልጽግና እንዲቀጥል ከማድረግ ውጭ ሌላ አላማ የለውም” ሲሉም ጠ/ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የአገሪቱ ሠራዊት ሌሎችን ለማጥቃትና ለመውረር እንደማያስብ የተናገሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ አገሪቱን ግን ይከለከላል ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ወይም ወደብ ያስፈልጋታል በሚል ሃሳብ ምክንያታቸውንም በዝርዝር ማቅረባቸው አይዘነጋም። አገራት ግን የጠ/ሚኒስትሩን የባህር በር ሃሳብ ወይም ጥያቄ በቀና የተመለከቱት አይመስልም። ኤርትራ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ የጠ/ሚኒስትሩን ሃሣብ የሚቃወሙና የማይቀበሉ መሆናቸውን በመግለጽ ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም።
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ከህዝብ ቁጥሯ ብዛትና ከተለያዩ የጎረቤት አገራት ወደቦች በቅርብ ርቀት ላይ መገኘቷን በመጥቀስና ሰጥቶ በመቀበል አግባብ የባህር በር ወይም ወደብ የምታገኝበት መንገድ መፈጠር እንዳለበት መናገራቸውን ተከትሎ፣ በርካታ ምሁራን በሚዲያ እየቀረቡ የጠ/ሚኒስትሩ ሃሳብ የሚደግፍና የሚያጠናክር ማብራሪያ ሲሰጡ ተደምጠዋል። ትላንት በኢቢሲ በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት ምሁር ኢትዮጵያ መድሃኒትና ነዳጅን ጨምሮ ወደ አገር ውስጥ ለምታስገባቸው የተለያዩ ምርቶች ወደብ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመው፣ ዓለማቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያን የባህር በር የማግኘት ፍላጎት ወይም ጥያቄ ይደግፉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
ጎረቤት አገራትም በንግግርና በውይይት ኢትዮጵያ የባህር ወደብ እንድታገኝ ትብብር ያደረጉ ዘንድ ምሁሩ ጥያቄ አቅርበዋል።
Source: Link to the Post