ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባሰለፈው ውሳኔ ማዘኗን ገለጸች። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ…

ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ባሰለፈው ውሳኔ ማዘኗን ገለጸች። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የውሃ አሞላል እና ስራዎችን በተመለከተ በትናንትናው እለት ያሳለፈው ውሳኔ እንዳሳዘናት ገልጻለች፡፡ የግድቡን አሞላልና እና ሌሎች ስራዎችን ጨምሮ የአባይ ወንዝ አያያዝና አጠቃቀምን በተመለከተ የአረብ ሊግ ለሚመለከታቸው የአፍሪካ ሀገራት መተው አለበት ብላለች ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የአባይ ወንዝ እና ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በአፍሪካ እንደሚገኙ ለሊጉ ማስታወስ የለብንም። ሊጉ የአለም አቀፍ ህግ መሰረታዊ መርሆችን ወደ ጎን በመተው የአንድ መንግስት ቃል አቀባይ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል” ብሏል፡፡ “የህዳሴ ግድብን ጉዳይን ወደ ፖለቲካ ለማሸጋገር የሚደረገው ጥረት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ወይም በህግ የተደገፈ ባለመሆኑ የወዳጅነት ግንኙነቱን አያሳድግም ወይም የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ የሚደረገውን ጥረት አይደግፍም” ብሏል፡፡ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች” በሚል መርህ የአህጉሪቱ ተቋም የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ፣ሱዳን እና ግብጽ ሚደረገውን የሶስትዮሽ ድርድር ሲያመቻች መቆየቱን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ፤ የአርብ ሊግ በጉዳዩ ላይ ያንጸባረቀው አቋም ትክክል አይደለም ሲልም ወቅሷል፡፡ ለድርድሩ መዘግየት እውነታው ግብጽ አሁንም በቅኝ ግዛት ዘመን ውል ላይ የተመሰረተ የውሃ ክፍፍል ለማስቀጠል ያላት ያልተቋረጠ አቋም እና ጉዳዩን አለም አቀፍ ለማድረግ የምታደርገው ጥረት መሆኑም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው ድርድር ቁርጠኛ መሆኑን ያስታወቀው የኢትየጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሊጉ ውሳኔዎችም ሆነ የግብጽ መግለጫዎች ግብጽ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በተደረገው ድርድር ላይ በቅን ልቦና ስለመገኘቷ አጠያያቂ እንደሚያደረገውም አንስቷል። በመጨረሻም እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጋቢት 2015 በተደረሰው ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ ታላቁን ህዳሴ ግድብ የመሙላትም ሆነ ስራዎችን የማከናወን ጉዳይ አጠናክራ ትቀጥለበታለች ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል የተፈረመው የ2015ቱ ስምምነት ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ እንዲሁም መርሆችን ባከበረ መልኩ ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶችን ለመጠቀም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ ዘገባው የአል ዐይን አማርኛ ነው።

Source: Link to the Post

Leave a Reply