ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ አድርጋለች፡፡ይህ በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እይታ ምን ማለት ይሆን?የምጣኔ ሃብት ባለሙያዉ ሙ…

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ አድርጋለች፡፡

ይህ በምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እይታ ምን ማለት ይሆን?
የምጣኔ ሃብት ባለሙያዉ ሙሸ ሰሙ በዚህ ዙሪያ ይህን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡-

ትልቅ እርምጃ ነው!! (ሙሼ ሰሙ)

ከቅርቡ ጊዜ ወዲህ የገንዘብ መግዛት አቅም እየወደቀ ነው ከሚል Speculation በመነሳት ያልተጠበቀና የናረ ፍላጎት በመፈጠሩ ምክንያት በተሽከርካሪና ቋሚ ንበረቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተከስቷል።

የተከሰተውን ከፍተኛ ጭማሪ ለማርገብ በተለይ በኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ ሁሉም የታክስ አይነቶች ሱር ታክስ፣ ኤክሳይዝ ታክስ ወዘተ በማንሳት 15 % ብቻ ተቀርጠው እንዲገቡ መፈቀዱ ትልቅ እርምጃ ነው።

በተሽከርካሪ ላይ የተወሰደው ዋጋ የማረጋጋት ውሳኔ በተጠና መልኩ በሌሎቹም ዘርፉች ቢቀጥል ሌሎች መፍትሔ የሚሹ ችግሮች እንደተጠበቁ ሆነው ኢኮኖሚያችን ላይ ትልቅ እመርታ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።

በነጻ ገበያ ስርዓት፣ ዜጎች ግብይታቸውንና አገልግሎታቸውን በሚያዋጣቸውና በሚጠቅማቸው መንገድ የማካሄድና እውቀታቸውን የመሸጥ መብት አላቸው።
ይህ ማለት ግን ሕግ፣ ስርዓት የማይገድባቸውና የዜጎች የጋራ ጥቅም የማይገዛቸውና ኋላፊነት የሌለባቸው ናቸው ማለት አይደለም።
አገልግሎታቸውን በተገቢው መንገድ የመስጠት፣ የትርፍ ሕዳጋቸውን ተመጣጣኝ የማድረግና ላተረፉት ትርፍ ተገቢውን መረጃ የማቅረብ፣ ተገቢውን ግብር እና መንግስታዊ ግዴታ መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ካልሆነ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ማረጋጋቱ የሚጠበቅ ነው። የዜጎችን የመግዛት አቅም በገንዘብ ከመደገፍ ጀምሮ፣ ሞኖፖሊንና ኦሊጎፖሊን በመቆጣጠርና ገበያው በምርት እስከ ማጥለቅለቅ የደረሰ እርምጃዎችን መውሰድ በምዕራባውያን ዘንድ የተለመደ አሰራር ነው።

የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አደጋና ስጋት ሲደቀንበት አደጋውን ለመቀልበስ ሲባልና ከጥቂት ነጋዴዎች ትርፍና ሐብት ማከማቸት ፍላጎት በላይ የሀገርና የሕዝብ ደህንነት በማስቀደም መንግስት ጣልቃ መግባታቸው የተለመደ ነው።
መንግስት በሕግ የተሰጡት ኢኮኖሚው ማቃኛ መንገዶች ተጠቅም የእርምት ይወስዳል።

ከተለመዱት የዋጋ ማረጋጊያ እርምጃ መካከል አንዱ የአቅርቦት ወይም የምርት ዋጋ ከመጠን በላይ ሲንር ተጓዳኝ እና ተመሳሳይ (Complementary, Supplementary ) ምርቶች ላይ የግብር ቅናሽ ማድረግ ነው ።
ለኑሮ እጅግ በጣም አስፈላጊ ምርት ሲሆኑ ደግሞ ተጓዳኝ ወይም ተመሳሳይ ምርቶችን አስመጥቶ ያለ ትርፍ ሕዳግና ያለ ተጨማሪ ወጭ ማከፋፈልና መሸጥም ሌላው ግሽበትንና ዋጋ ማረጋግያ መንገድ ነው።

በነዳጅ ከሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ጋር ሲወዳደር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ዋጋ ከ50 በመቶ በላይ ቅናሽ ይኖረዋል።
ውሳኔው የአየር ብክለት ከመቀነስ፣ በርካታ መለዋመጫን ከማስቀረትና ከዘይትና ከነዳጅ ግዢ ከመታደጉም በላይ ያበጠውን የተሽከርካሪ ዋጋ እንደሚያስተነፍሰው ጥርጥር የለው። ይበል የሚያሰኝ ትልቅ እርምጃ ነው።

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ (Windfall gain) ነው አብዛኛው የተሽከርካሪ ነጋዴ ሕጋዊ ደረሰኝ እየሰጠና ትርፉን እያሳወቀ አይደለም።
ለምሳሌ ዛሬ ላይ አንድ ሲዙኪ ዲዛየርን ስም ለማዞር መንገድ ትራንስፖርት የሚገምተው ከ750 ሺህ እስከ 1 ሚሊየን ብር ነው።
ተጨማሪ ወጭዎች ተደማምረው የተሽከርካሪው የሽያጭ ዋጋው በአማካይ እስከ ከ1.2 ሚሊየን ብር ቢደርስ፣ ተሽከርካሪው ገበያ ላይ አሁን የሚሸጥበት ዋጋ 2 ሚሊየን 100 ሺህ ሰለደረሰ ሻጩ ከአንድ ሚሊየን እስከ አንድ ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ ብር ድረስ ትርፍ እያገኙ በመሸጥ ላይ ናቸው።
በነጻ ገበያ ስርዓት በፈለጉት ዋጋ መሸጥ መብት የመሆኑን ያህል አብረውት የሚመጡ ግዴታዎች ስላሉት ለተገኘው ገቢ የትርፍ ግብርና ለተፈጠረው እሴት ደግሞ ተ.እ.ት መክፈል የዜግነት ግዴታ ነው።

የኑሮ ውድነት አናቱ ላይ እያናጠረበት ከሚያገኛት ደሞዝና ጥቅማጥቅ ላይ እግር በእግር እየተከታተለ እስከ 35 በመቶ የገቢ ግብር የሚያስከፍል መንግስት ከ50 በመቶ እስከ 100 በመቶ እያተረፉ ገቢን በመሰወርና ደረሰኝ በመከልከል ግዴታቸውን የማይወጡት ተሽከርካሪ አስመጭዎችን ቸል ሊል አይገባም።

የትርፍ ግብር እና ተ.እ.ት ክፍናን ላላሳወቁና በሰወሩ ላይ አስተማሪ በሆነ መልኩ ትርፍ ግብር ከነመቀጫው ማስከፈል አለበት።

ሁሉም ሰው በሀገሩ ላይ በዜግነቱ እኩል ነው። ተጠቃሚ በሆነበትና ሐብት በአፈራበት ልክ ትርፉን በማሳወቅና ግብር በመከፍል የዜግነት ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያያን
መስከረም 07 ቀን 2015 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply