ኢትዮጵያ የዉጭ ጣልቃ ገብነትን ከመከላከል ረገድ አብዛኛዉ ዲፕሎማቶቿ ላይ ክፍተኛ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ተባለ፡፡የተወሰኑ ዲፕሎማቶች የአገራቸዉን ጥቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያስረዱ ቢ…

ኢትዮጵያ የዉጭ ጣልቃ ገብነትን ከመከላከል ረገድ አብዛኛዉ ዲፕሎማቶቿ ላይ ክፍተኛ ክፍተቶች ይስተዋላሉ ተባለ፡፡

የተወሰኑ ዲፕሎማቶች የአገራቸዉን ጥቅም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያስረዱ ቢገኙም አብዛኞቹ ግን አቅማቸዉን አሟጠዉ እየሰሩ አይደለም ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ አገር ብዙ ስራዎችን መስራት እንዳለባትና በተለይም በዲፕሎማሲዉ ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥታ ልትንቀሳቀስ እንደሚገባም ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ተናግረዋል፡፡

አሁን የሃያላን አገራት ዓይን ሁሉ የሚያማትረዉ ወደ ኢትዮጵያ ነዉ፤ በአገር ዉስጥ ባለዉ የፖለቲካ አለመረጋጋት፤ በኢትዮ ሱዳን የድንበር ዉዝግብና በህዳሴ ግድብ ድርድር ምክንያት ያላቸዉ መረጃ የተሳሳተና የተንሸዋረር እንደሆነ በርካታ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ብዙዎች ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ወቅት እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ነዉ፤ምክንያቱም በአገር ዉስጥ በነበረዉ የህግ ማስከበር ዘመቻ ምእራባዉያኑ የተሳሳተ መረጃን በመያዝ የአገሪቱን እጅ ለመጠምዘዝ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ያነሳሉ፡፡

እናም ኢትዮጵያ እንደ አገር ብዙ ስራዎችን መስራት እንዳለባትና በተለይም በዲፕሎማሲዉ ዘርፍ ላይ ትኩረት ሰጥታ ልትንቀሳቀስ ይገባታል ይላሉ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን፡፡

በጎንደር ዩንቨርሶቲ የአለም አቀፍ ግንኙነትና ጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ምንቺል መሰረት ፤ ኢትዮጵያ እጇ ላይ ያሉ እዉነታዎችን በተገቢዉ መንገድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እያደረሰች አይደለም፤ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ አምባሳደሮች በትኩረት እየሰሩ አይደለም ብለዋል፡፡

እናም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲፕሎማቶቹ ላይ ግፊት በማድረግ በትኩረት እንዲቀሳቀሱ ማድረግ እንዳለበትም አንስተዋል፡፡

አዉሮፓዉያኑም ሆኑ አሜረካ በታሪክ መረዳት እንደሚቻለዉ አንዲት አገር በአገር ዉስጥ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ሲገጥማት ፤እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ይጠመዝዛሉ አሁንም ይህንኑ አካሄድ ነዉ እየተከተሉ ያሉት የሚሉት ደግሞ የወሎ ዩንቨርሲቲዉ የታሪክ ምሁሩ ዶክተር አለማየሁ እርቅ ይሁን ናቸዉ፡፡

ዲፕሎማሲ ብቻዉን በቂ ባለመሆኑ በአገር ዉስጥ ያለዉን ልዩነት ማስወገድ ይገባልም ብለዋል ዶ/ር አለማየሁ፡፡

እኛም መንግስት የዉጭ ጣልቃ ገብነቱን እንዴት እየተከታተለዉ ነዉ ስንል የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የጠየቅን ሲሆን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሶስት ጉዳዮች ምክንያት የተለያዩ አገራት ኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡

እነዚህም የህዳሴ ግድብ፤ የኢትዮ ሱዳን ድንበርና በትግራይ ያለዉ የህግ ማስከበር ነዉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ሱዳንም ሆነች ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ የዲፕሎማሲ የበላይነትን ለመያዝ ከፍተኛ አመራሮችን ጭምር ወደ ተለያዩ አገራት በማሰማራት የዲፕሎማሲ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ኢትዮጵያስ ከዚህ አኳያ ምን እሰራች ነዉ ወደፊትስ እንደ አገር ምን ታስቦ ይሆን፤ ስንል አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጠይቀናል፡፡

በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በምክትከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን እና በፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘዉዴም ጭምር ከበርካታ አገራት መሪዎች ጋር ዉይይቶች እየተካሄዱ ነዉ ብለዋል፡፡

የተለያዩ አገራት በኢትዮጵያ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸዉ በር ከፋች ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የዲፕሎማሲ ስራ መዳከም እንደሆነና ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ወክለዉ በተለያዩ ዓለማት የሚገኙ ዲፕሎማቶች አቅማቸዉን አሟጠዉ ባለመስራታቸዉ ነዉ ይባላል፡፡

በዲፕሎማቶቹ ላይ ክፍተት መኖሩን ያልሸሸጉት አምባሳደር ዲና፤ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አስቸጋሪ ጊዜ በመሆኑ ሁሉም ዲፕሎማቶች የአገራቸዉን ጥቅም ከምን ጊዜዉም በላይ እንዲያስጠብቁ አዲስ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል ነዉ ያሉት፡፡

በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን በአገራቸዉ ጉዳይ የሚገቡ ሃይሎችን በመቃወም እያደረጉት ላለዉ አገራዊ ፍቅር ምስጋናቸዉን ያቀረቡት ቃል አቀባዩ፣ ኢትዮጵያ ዲፕሎማቶቿ ጠንክረዉ እንዲሰሩ ግፊት እያደረገች እንደምትገኝም አስታዉቀዋል፡፡

በአባቱ መረቀ
መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply