ኢትዮጵያ 75 ሚሊዮን ዶላር የውጪ አየር መንገዶችን ገንዘብ መያዟ ተገለጸ

ሰኞ ሰኔ 13 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ወደ አዲስ አበባ የሚበሩ የውጭ አየርመንገዶችን የትኬት ሽያጭ ክፍያ 75 ሚሊዮን ዶላር አግታ መያዟን አለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር (IATA) አስታወቀ፡፡

ወደ አዲስ አበባ የሚበሩ የተለያዩ አየርመንገዶች በኢትዮጵያ በብር የሸጡትን የአየር ትኬት ሽያጭ በዶላር ቀይረው ወደ አገራቸው ለመላክ እንዳልቻሉ ገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ናይጄሪያ 450 ሚሊዮን ዶላር፣ ዚምባብዌ 100 ሚሊዮን ዶላር፣ አልጄሪያ 96 ሚሊዮን ዶላር፣ ኤርትራ 79 ሚሊዮን ዶላር የውጭ አየርመንገዶች ገንዘብ መያዛቸውን የአለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣና ም/ል ፕሬዝደንት ካሚል አልዋላዲ በኳታር ዶሃ በመካሔድ ላይ በሚገኘው የማህበሩ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ አስታውቀዋል፡፡

አልዋላዲ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አንዳንድ የአፍሪካ አገራት በገጠማቸው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት አየርመንገዶቹ ገንዘባቸውን እንዲያወጡ እንዳልፈቀዱላቸው ተናግረዋል፡፡

ችግሩ የአየር ትራንስፖርት ዘርፉን ይጎዳል ያሉት አልዋላዲ፤ ከእነዚህ የአፍሪካ አገራት ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሆኑም መግለፃቸውን ኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ ዘግቧል፡፡

ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር 78ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply