ኢትዮ ልዩ!ድንቃድንቅ መረጃዎች ከኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 1፤በሃሰት መሞቱን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲለቀቅ ያደረገው ግለሰብ እናቱ ራሳቸውን ስተው ሆስፒታል እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡…

ኢትዮ ልዩ!

ድንቃድንቅ መረጃዎች ከኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8

1፤በሃሰት መሞቱን በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንዲለቀቅ ያደረገው ግለሰብ እናቱ ራሳቸውን ስተው ሆስፒታል እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡

ነገሩ የተሰማው ከወደ ብራዚል ነው፡፡
ባልታዘር የተባለው የ60 አመት ጎልማሳ በዲኮር ስራ ተሰማርቶ ህይወቱን ይመራል፡፡ በዚህም የብዙዎችን ሰርግና ልደት አድምቋል፡፡

የእርሱን ግን የሰርጉን ሳይሆን ቀብር ስነ-ስርዓቱን ለማድመቅ ያሰበ ይመስላል፡፡

ግለሰቡ በህይወት ሲለይ ማን በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ በመፈለግ፣በመጀመሪያ በጠና ታሞ ሆስፒታል እንደገባ ራሱ ጽፏል፣በኋላም በተባባሪ ጓደኛው በኩል እንደሞተ ያስነግራል፡፡

ይህ ሲሆን ከአስከሬን ሳጥን እስከ መኪና ዲኮር ድረስ ራሱ አዘጋጅቶ ነው፡፡
ግለሰቡ ይቀበርበታል ተብሎ ወደ ተዘጋጀው ስፍራ እስከ 500 የሚሆኑ ሰዎች መታደማቸው የተነገረ ሲሆን እራሱን ደብቆ እሱም እዛው መሃላቸው ሲታዘብ ነበር ተብሏል፡፡

በሁኔታው ተደናግጠው ራሳቸውን የሳቱት እናቱ በዓሁኑ ወቅት ሆስፒታል እንደሚገኙና እርሱም አስታማሚ ሆኖ ሆስፒታል እንደሚገኝ ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
(በሔኖክ ወ/ገብርኤል)

2፤በአሜሪካ በቴክኒክ ችግር ምክንያት ለሁለት አመታት አልጠፋም ያሉ መብራቶች ግርታን ፈጥረዋል፡፡

ይህ የሆነው በአሜሪካዋ ግዛት ማሳቹሴት በሚገኝ አንድ የሀይስለኩል ት/ቤት ሲሆን 7 ሺህ የሚሆኑ ስማርት ላይቶች ለ24 ሰዓታት እየበሩ እንሆ ሁለት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ት/ቤቱ በመጀመሪያ አካባቢ አምፖሎች አልጠፋ ሲሉ ቀለል ተደርጎ ነበር የተመለከተው፤በኋላ ሲጣራ ግን እነዚህን ስማርት ላይቶች የገጠመው ድርጅት በወቅቱ ማብሪያ ማጥፊያ ሲስተሙን አብሮ እንዳልሰራው ተደርሶበታል፡፡

ት/ቤቱ መጠኑን ባይገልጽም በእነዚህ ላይቶች ምክንያት አላግባብ በባከነው ሃይል ምክንያት ለከፍተኛ ክፍያ መዳረጉን አስታውቋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለእነዚህ ላይቶች መላ ይዘይድ ዘንድ ሪፍሊክስ ላይት ግሩፕ ጥያቄ ቀርቦለታል ሲል ዩፒ አይ ዶት ኮም ጽፏል፡፡
(በአቤል ደጀኔ)

3፤5ቷ ዶላር 107 ሺህ ዶላር እንዲገኝ ምክንያት ሆነች፡፡

ማቲው ስፓውልዲንግ በአሜሪካ ሚቺጋን ነዋሪ የሆነ የ42 ዓመት ጎልማሳ ነው፡፡

ሰሞኑን አን አርቦር ውስጥ ሳውዝ ስቴት በተባለው ጎዳና ከሚገኝ ሞቢል የነዳጅ ማደያ ጎራ ብሎ ነዳጅ ከቀዳ በኋላ 5 ዶላር ይመለስለታል፡፡

በአካባቢው ወደሚገኝ የገበያ አዳራሽ ጎራ ሲልም እግረ መንገዱን በዛች 5 ዶላር የሚቺጋን ሎተሪ ፋስት ጌም ቲኬት ይቆርጣል፡፡

ዕጣው ሲወጣ ታዲያ ያቺ ከነዳጅ ቅጂ የተመለሰች 5 ዶላር የ107 ሺህ 590 ዶላር የጃክፖት አሸናፊ አድርጋዋለች፡፡ “እንደ አጋጣሚ ነው ሎተሪውን የቆረጥኩት፡፡

ብዙ ጊዜ የፋስት ካሽ ጌም ሎተሪ የመቁረጥ ልማድ የለኝም” የሚለው ማቲው አሸናፊነቱን ያረጋገጠውም የገበያ አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡

“በወቅቱ በጣም እየጮህኩኝ ደስታዬን ስገልፅ እዛ የነበሩትን ሰዎች የረብሽኳቸው ይመስለኛል፡፡

ራሴን ስቼ ነበር ለማለት ይቻላል” ሲልም ስሜቱን ገልጿል፡፡ በገንዘቡ ምን ሊያደርግበት እንደፈለገ ተጠይቆም ለጊዜው የተለየ ዕቅድ ስለሌለው በባንክ እንደሚያስቀምጠው ተናግሯል፡፡(በምስጋናው ታደሰ)

4፤ከከባድ ወንጀለኛ ጋር ስሙ የተመሳሰለዉ ግለሰብ በስህተት 3 ጊዜ ለእስር ተዳረገ፡፡

የ46 ዓመቱ ኮሎምቢያዊ ግለሰብ ባለፉት 13 ዓመታት ዉስጥ ከአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪ ጋር ስሙ በመመሳሰሉ የተነሳ ለ3 ጊዜ ያህል ለእስር እንደተዳረገ ተነግሯል፡፡

ሬኒ ማርቲኔዝ ጉቴሬዝ የተባለዉ ይህ ግለሰብ የፔሩ ዜግነት ካለዉ እና በአገር ዉስጥ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዕጽ ማዘዋወር ወንጀል ከሚፈለገዉ ቀንደኛ ወንጀለኛ ጋር ስሙ ተመሳሳይ ነው፡፡

ይህ ግለሰብ ታዲያ የታመሙ አባቱን ለመጠየቅ ባደረገው ጉዞ ከአውሮፕላን ሲወርድ በፖሊስ ተይዞ እስር ቤት ሊገባ ችሏል፡፡

ግለሰቡ ለ 2 ጊዜ ለእስር ከተዳረገ በኋላ የወሰነዉ ዉሳኔ ቢኖር ወደ አሜሪካ መሸሽ እና ኑሮዉን እዛ ማድረግ ነበር፣ ይሁን እንጂ ሽማግሌ አባቱ በጠና መታመማቸዉን ተከትሎ ወደ ትዉልድ ሀገሩ ሲያቀና ይህ ጉዳይ ሊከሰት እንደሚችል እርግጠኛ እንደነበርም ተናግሯል፡፡

ልክ አየር ማረፊያዉ ዉስጥ አዉሮፕላኑ እንዳረፈ መታወቂያዉን በኢንተርፖል አባላት የተጠየቀዉ ሬኒ ስሙ እሱ መሆኑን በመረጋገጡ ወዲያዉ ወደ ተለመደዉ እና ባለፉት 13 ዓመታት ዉስጥ በተደጋጋሚ ሲታሰር ወደቆየበት እስር ቤት ሊወሰድ ችሏል፡፡

በሚያሳዝን ሁኔታ በእስር ላይ እያሉ አባቱ ህይወታቸዉ በማለፉ ለመሰናበት እና ሀዘኑን ለመወጣት እንኳን እድል እንዳላገኘ የሚገልጹት ቤተሰቦቹ ፣ የፔሩ መንግስት ይህ ግለሰብ የሚፈልጉት ወንጀለኛ አለመሆኑን ተረድተዉ ነጻ ይለቁታል በሚል ተስፋ እየጠበቁ መሆናቸዉን የዘገበዉ ኦዲቲ ሴንትራል ነዉ፡፡
(እስከዳር ግርማ)

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ወቅታዊ አዳዲስ መረጃዎችና ፕሮግራሞችን ለማግኘት ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

Twitter https://twitter.com/EthioFM

YouTube https://www.youtube.com/…/UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos

Facebook https://www.facebook.com/onelovebroadcast

Website https://ethiofm107.com/

ያሎትን አስተያየት እና ጥያቄ በአጭር መልዕክት 6321 ላይ ይላኩልን።
ከኛ ጋር ስለሆናችሁ ከልብ እናመሰግናለን።

Source: Link to the Post

Leave a Reply