ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ግማሽ ዓመት 43 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም፤ ባለፈው መንፈቅ ዓመት 42.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። ኢትዮ ቴሌኮም በዚሁ ጊዜ ውስጥ የደንበኞቹ ቁጥር 74.6 ሚሊዮን መድረሱንም ገልጿል።   

ኢትዮ ቴሌኮም ይህን የገለጸው የ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የስራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 14፤ 2016 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ተቋሙ በዚህ ጊዜ ውስጥ ያስገባው ገቢ፤ ከእቅዱ 98 በመቶውን ያሳካ መሆኑን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር 26 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ያገኘው ገቢ 33.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን በወቅቱ ያስመዘገበው ትርፍ ደግሞ 9.72 ቢሊዮን ብር ነበር። ተቋሙ ዘንድሮ በግማሽ ዓመት ብቻ 11 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ፍሬሕይወት ይፋ አድርገዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው መንፈቅ ካስገባው ገቢ ውስጥ 41 በመቶ የሚሆነውን ያገኘው ከሚሰጠው የስልክ የድምጽ አገልግሎት መሆኑ በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። የኢንተርኔት እና ዳታ አገልግሎት፤ ከገቢው 25.7 በመቶውን በመያዝ በሁለተኛነት ተቀምጧል።

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ካሉት 74.6 ሚሊዮን ደንበኞች ውስጥ 71.7 ሚሊዮን የሚሆኑት የሞባይል የድምጽ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው። የሞባይል ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት የሚጠቀሙ የኩባንያው ደንበኞች ቁጥር ደግሞ 36.4 ሚሊዮን መሆናቸውን ኩባንያው አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

Source: Link to the Post

Leave a Reply