ኤርትራ 60 በመቶ የሚሆነው የኢሮብ ብሄረሰብ መሬት በቁጥጥር ስር ማዋሏ ተነገረ፡፡

በትግራይ ክልል የሚገኘው የኢሮብ ብሄረሰብ 60 በመቶ መሬት በኤርትራ ቁጥጥር ስር ተይዟል መባሉን ኢትዮ ኤፍ ኤም ሰምቷል፡፡
ይህንን ያለው ደግሞ ኢሮብ አኒና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

የድርጅቱ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ተስፋይ አብዓላ ከጣብያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት ከሆነ በወረዳው ካሉ ስድስት ቀበሌዎች ሁለቱ በከፊል ሁለቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ኤርትራ መጠቅላሉን ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት መሬቱን መውሰዱም ብቻ ሳይሆን በብሄረሰቡ ተወላጆች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳቶችን እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተለይም መንገዱን በመዝጋቱ የተነሳ ምንም ዓይነት እርዳታ ወደ አካባቢው እንዳይደርስ በማድረጉ ብሄረሰቡ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ቀውስ ውስጥ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ ምንም ዓይነት ማህበራዊ አገልግሎት እያገኘ አይደለም የሚሉት አቶ ተስፋይ ከዛ ባለፈም በግዴታ ኤርትራዊ ናችሁ እየተባሉ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡

“አከባቢው ወደ ኤርትራ ተጠቃሏል ከዚህ ወዲህ ኤርትራዊ ናችሁ ልጆቻቹም አስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት መላክ ይኖርባችሃል” እየተባሉ ማስገደድ መጀመራቸውንም አንስተዋል፡፡

የኤሮብ መሬት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የኤርትራ አካል ሆኖ አያውቅም ይሁን እንጂ የኤርትራ መንግስት ድንበር ተሻግሮ መሬት መውረሩ የፌደራል መንግስት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም ጦርነቱ ከተጀመረበት ግዜ አንስቶ ምንም ዓይነት ሰብዓዊ እርዳታ ያላገሳ ህዝብ በዚህ ሁኔታ ውስጥ መገኘቱ አሳዝኖናል ብለውናል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስትም ተወሮ የሚገኘውን መሬት በማስለቀቅ ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በአቤል ደጀኔ

መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply