ኤጀንሲው የመንጃ ፍቃድ እገዳው ለጊዜው እንዲቆም መወሰኑን ገለጸ

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) አሽከርካሪዎች ሕግ ሲጥሱ በፖይንት ፔናሊቲ ሥርዓት (Point Penality) መሰረት ተደራሽ እየተደረጉ፤ ነጥቡ 17 ሲደርስ እንዳያሽከረክሩ የመንጃ ፈቃድ እግድ የማድርግ ሥራው ላተወሰነ ጊዜ እንዲቆም መወሰኑን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ ገለጸ፡፡

የመንጃ ፈቃድ እገዳው ከሰኔ 30 ቀን 2014 ጀምሮ እንዲቆም የተደወሰነ ሲሆን፤ የቆይታ ግዜው ግን እንዳልታወቀ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት የኮሚዪኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ብርሃኑ ኩማ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

የመንጃ ፈቃድ እገዳው እንዲቆም የተወሰነው ኤጀንሲው ሊያጠናቸው የመሚገቡ በርካታ ችግሮች ስለተስተዋሉ ነው የተባለ ሲሆን፤ ስህተት የሚፈጽሙ አሽከርካሪዎች ግን እንስካሁኑ ነጥባቸው 17 ሲደርስ እንዲያሽከረክሩ ባይታገዱና መንጃ ፈቃዳቸውን ለማውጣት የተህድሶ ሥልጠና ባይወስዱም ቅጣቱና የጥፋት ነጥቡ እየተመዘገበ ይቀጥላል ሲሉ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

የቅጣት ሥርዓቱ እያስገኛቸው ያሉ አዎንታዊ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ ለጊዜዉ የእግድ ሥራው እንዲቆም ለመወሰን ካበቁ ጉዳዮች መካከል፤ ሲስተሙ ሲለማ ምን ችግሮችን ለመፍታት ታሳቢ እንዳደረገ፣ የሚሸፍናቸው ሥራዎች፣ የተሰራበት ቋንቋ፣ ሲስተሙን ማን እየተጠቀመበት እንዳለ እና እስካሁን እነማን በሥርዓቱ ላይ ድርሻ እንደነበራቸው እና ምን መሆን እንዳለበት በኤጀንሲው አለመታወቅ ይገኙበታል።

በተጨማሪም፤ አሽከርካሪዎች ከታገዱ በሓላ የተሃድሶ ሥልጠና የሚወስዱበት ኹኔታ ላይ የተሟላ እና የተደራጀ አተገባበር አለመኖሩ እና ሲስተም ውስጥ ያልተመዘገቡ አሽከርካሪዎች የማይታገዱ በመሆኑ በዜጎች መካከል የፍትሃዊነት ችግር መፍጠሩ ተገልጿል።

ብርሃኑ ሥርዓቱ ተግባራዊ ከተደረገ አንስቶ እስካሁን ስንት አሽከርካሪዎች ተቀጥተዋል በሚል ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄም ብዛታቸውን ተደራሽ እንዳላደረጉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ የፖይንት ፔናሊቲ ሲስተም (Point Penality)ን ሥራ ላይ አዉሎ በአሽከርካሪዎች የሚፈፀሙ ጥፋቶች በደንቡ መሰረት እየተመዘገቡ ነጥቡ 17 ሲደርስ በሲስተሙ እንዳሽከረክሩ የማድርግ ተግባር ሲያከናውን መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply