እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ላይ ምስክር ለማሰማት መጋቢት 29 እና 30 ቀን 2013 ቀጠሮ ተሰጠ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም…

እስክንድር ነጋን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ላይ ምስክር ለማሰማት መጋቢት 29 እና 30 ቀን 2013 ቀጠሮ ተሰጠ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ ታህሳስ 17 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ሕገ መንግሥታዊ እና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የሚገኙ አራት ተከሳሾች ትናንት ታህሳስ 16 ቀን 2013 ዓ.ም የተከሰሱበትን ወንጀል ክደው በመከራከራቸው የዐቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማት ቀጠሮ ሰጥቷል። በችሎት ውሎውም ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃል እንዲሰጡ ተደርጓል። ተከሳሾቹም ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለዋል። ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾቹ ወንጀሉን ክደው ስለተከራከሩ ምስክር ማሰማት ይፈቀድልኝ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። ችሎቱም መጋቢት 29 እና 30 ቀን 2013 ዓ.ምን ጨምሮ በሚያዚያ ወር ውስጥ በድምሩ ዐሥር ቀናት ያህል ምስክር እንዲያሰማ ፈቅዷል። ተከሳሾቹ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 22 ቀን 2012 የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በነበረው ሁከት እና ብጥብጥ ብሔር እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት ቀስቅሰዋል ፣ በውጤቱም የሰው ሕይወት ማለፍ፣ የበርካታ ንብረት ውድመት እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች መከሰሳቸው አይዘነጋም፡፡ በተያያዘ ዜና ዐቃቤ ሕግ የችሎት መድፈር ክስ ቢመሰርትም ፍርድ ቤቱ በማስጠንቀቂያ አልፎታል ሲል ነው ኢብኮ የዘገበው፡፡ በችሎቱ ላይ የተራዘመ ቀጠሮ የተሰጠበት ምክንያት ሆንተብሎ በእስር ላይ ያሉት የባልደራስ መኢአድ ቅንጅት ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ፣ስንታየሁ ቸኮል፣አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ነው በሚል በተከሳሾች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቧል። የችሎት ታዳሚዎች፣የተከሳሽ ቤተሰቦች፣ የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎችም ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ረዥም ቀጠሮ ተቃውመውታል፤ በፖሊስ አማካኝነት ከችሎት እንዲወጡ መደረጉንም ፓርቲው በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ካሰፈረው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በችሎቱ የተራዘመ ቀጠሮ የተከፉት እነ እስክንድር ነጋ፣ስንታየሁ ቸኮል፣አስቴር ስዩምና አስካለ ደምሌ በፍ/ቤቱ የተቀላጠፈ ፍትህ እንዲያገኙ ቀድመው ሲያሳስቡትና ሲጠይቁት የነበረው ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን የሚያመላክት ፖለቲካዊ አካሄድ እየተሄደ እንደሆነ ገልፀዋል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply