
እነ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ ዶ/ር ወንዶሰን አሰፋ፣ ፋኖ መንበር አለሙ እና ሌሎች በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ በሁከት እና ብጥብጥ እንዲሁም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል በሜክሲኮ ማቆያ የሚገኙ እስረኞች የርሃብ አድማ መጀመራቸውን አስታወቁ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል (አሚማ) ግንቦት 8/2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ በሁከት እና ብጥብጥ እንዲሁም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል በሜክሲኮ ማቆያ የሚገኙ እነ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከግንቦት 8/2015 ጠዋት ጀምሮ የርሃብ አድማ መጀመራቸውን አስታውቀዋል። የእነ ረዳት ፕ/ር ሲሳይ አውግቸው፣ ፕ/ር መዓረጉ ቢያበይን፣ ዶ/ር መሰረት ቀለመ ወርቅ እና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋውን ጨምሮ እስከ 40 የሚደርሱ በሁከት እና ብጥብጥ እንዲሁም በሽብር ወንጀል ተጠርጥራችኋል በሚል በአዲስ አበባ ሶስተኛ ጣቢያ የሚገኙ እስረኞች ለ3 ቀናት የሚቆይ የርሃብ አድማ መጀመራቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ግንቦት 8/2015 ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሜክሲኮ ለጥየቃ ያቀኑ ቤተሰቦች ለአሚማ ያደረሱት መረጃ እንዳመለከተው እነ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው፣ ዶ/ር ወንዶሰን አፋ፣ ፋኖ መንበር አለሙ እና ሌሎች በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ በሁከት እና ብጥብጥ እንዲሁም በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል በሜክሲኮ ማቆያ የሚገኙ እስረኞች የርሃብ አድማ ጀምረዋል። የርሃብ አድማ ስለጀመርን በሚል የተወሰደላቸውን ምግብ መልሰዋል ሲሉ ቤተሰቦች ተናግረዋል። እስረኞቹ የርሃብ አድማውን ማድረግ የጀመሩበት ዋነኛ አላማም በተለይም በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በአማራ ላይ የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ እየፈጸመ ያለውን የጅምላ እስር፣ ወከባ እና አፈና በአስቸኳይ እንዲያቆም ለመጠየቅ ነው።
Source: Link to the Post