እናት ባንክ በጎዳና ፅዳት ላይ የተሰማሩ እናቶችን የገቢ አቅም በዘላቂነት ለማጠናከር የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል።
እናት ባንክ ከእንደዜጋ ማህበራዊ እንደራሴ እና አነጋ ኢንጅነሪንግ ጋር በመሆን የእናቶችን የገቢ አቅም ማሳደግ መሠረት ያደረገ የሶስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት በትናንትናው ዕለት ተፈራርሟል።
እናት ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ፅዳት ላይ የተሰማሩ እናቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን ችለው እራሳቸውን ቤተሰቦቻቸውንም እንዲያግዙ ለማድረግ “እናት ለእናት” የተሰኘ ፕሮጀክት ነድፎ በሶስት ወር ሰርቶ ተግባራዊ ማድረጉን የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ገነት ሀጎስ ተናግረዋል።
ባንኩ በዚህ ፕሮጀክት ተሳታፊ ለነበሩ በጎዳና ፅዳት ላይ ለተሰማሩ 60 እናቶችም የበዓል ስጦታ ማበርከቱንም ነው የገለፁት።
ባንኩ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ አራት የበጎ አድራጎት ተቋማትም የፋይናንስ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት ነህምያ ኦቲዝም ማዕከል ፣ ስለ እናት የበጎ አድራጎት ድርጅት ፣ ሳራ ካኒዜሮ ቻይልድ ማይንደርስ ማህበር እና ትኩረት ለሴቶችና ለህፃናት ማህበር ናቸው ።
ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ የሴቶችን የፋይናንስ አካታችነት የሚያጎለብት አሠራርና የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ላይ ይገኛል ተብሏል።
በእስከዳር ግርማ