እናት ፓርቲ በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ቦጬሳ በተባለ ቦታ “ለስብሰባ የተጠሩ” የሲዳማ ማንነት ያላቸው ወገኖቻችን በጥይት እሩምታ መገደላቸው እንዳሳዘነው ገለጸ፤ ቦጬሳ የጎሳ…

እናት ፓርቲ በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ቦጬሳ በተባለ ቦታ “ለስብሰባ የተጠሩ” የሲዳማ ማንነት ያላቸው ወገኖቻችን በጥይት እሩምታ መገደላቸው እንዳሳዘነው ገለጸ፤ ቦጬሳ የጎሳ ፖለቲካችን ተረኛ የማፅዳት ግንባር የተደረገ ስለመሆኑ በመግለጫው አስፍሯል። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ/ም አዲስ አበባ ሸዋ እናት ፓርቲ በወቅታዊ በቦጬሳ የተፈጸመውን ግድያ በተመለከተ የሚያወግዝ መግለጫ አውጥቷል። ሙሉ መግለጫውም የሚከተለው ነው:_ ቦጬሳ የጎሳ ፖለቲካችን ተረኛ የማፅዳት ግንባር! ሥርዓቱ ኮትኩቶ ያሳደገውና አኹንም የአብዛኛው የሀገራችን ችግሮች ምንጭ የሆነው የጎሳ ፖለቲካ ቦታ እየቀያየረ የዜጎቻችንን ሕይወት እየቀጠፈና እያመሰቃቀለ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ጎሰኝነት ባሰከራቸዉ ግለሰቦችና ቡድኖች ዕለት ዕለት እልቂት ማስተናገድ ከጀመረች ዘለግ ያለ ጊዜ ያስቆጠረች ቢሆንም “ለውጥ መጣ” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዓመታት ግን በከፋ ሁኔታ እየተመሰቃቀለችና ሕልውናዋም ስጋት ላይ እየወደቀ መጥቷል፡፡ ድሮ በእርሻ ወይንም በግጦሽ መሬት ምክንያት ከዕለት ግጭት የማያልፈው አለመግባባት ዛሬ ላይ በተደራጀና በተጠና መልኩ ንጹሓን ኢትዮጵያውያን ሀይ ባይ ሳይኖር በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በእጅ አዙር በተደራጁ ታጣቂዎች በማንነታቸው ተለይተው ሲጨፈጨፉ መስማት ጆሯችን ተላምዶት የት ቦታና፣ የየትኛው ጎሳ፣ ስንት ሰው የሚለውን ለማወቅ ካልሆነ በስተቀር ጉዳዩ እንደ ሕዝብ የማያስደነግጠን ደረጃ ላይ ከመድረሱ የባሰ አስጊ ነገር የለም፡፡ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ ጊዜያት በተፈጸሙት ማንነት ተኮር ፍጅቶች ትርጉም ያለው እርምጃ ሊወሰድ ባለመቻሉ ቦታው እየተለዋወጠ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ ምድራችን የልጆቿን ደም እንድትጠጣ ተደርጓል፡፡ እናት ፓርቲ ኢትዮጵያ አየተከተለችው ያለውን ይህን አጥፊ ጎዳና በተከታታይ ጊዜያት በጽኑ ያወገዘ ሲሆን በዚህ ጉዳይ እጃቸዉ ያለበት የመንግሥትና ሌሎችም አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ አጥብቆ ጠይቋል፡፡ ይሁን እንጅ በተጠና መልኩ የሚከናወነዉ የማፅዳት ተግባር መፍትሄ ከማግኘት ይልቅ ከሰሞኑ ግንባር ቀይሮ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ቦጬሳ በተባለ ቦታ “ለስብሰባ የተጠሩ” የሲዳማ ማንነት ያላቸው ወገኖቻችን በጥይት እሩምታ መገደላቸው የጎሳ ፖለቲካው ሥር መስደድና የችግሮቻችን ዕለት ከዕለት መወሳሰብ ኹነኛ ማሳያ ነው፡፡ አገር እንድትለማመድ እየተገደደች ካለችው የልጆቿ ፍጅት ልትላቀቅ እንደሚገባ እናት ፓርቲ አጽንኦት ሰጥቶ ሊገልጽ ይወዳል፡፡ ስለሆነም፡- 1.የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በፍጅቱ ዙሪያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቂ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡ 2. ከጉዳዩ ጀርባ እጃቸዉ ያለበት የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ይህም መደረጉ በይፋ እንዲገለጽ እንጠይቃለን፡፡ 3. በአኹኑ ሰዓት ችግሩ ከተፈጠረበት ቦጬሳ አካባቢ አልፎ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉ ወረዳው ወደከፋ ያለመረጋጋትና የባሰ ቀውስ ውስጥ የመግባት አዝማሚያ እየታየ ስለሆነ መከላከያ ሰራዊት በአካባቢው ያለውን ሁኔታ እንዲቆጣጠር እናት ፓርቲ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡ በመጨረሻም በዚህ ፍጅት ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ ወገኖቻችን መጽናናትን እንመኛለን፡፡

Source: Link to the Post

Leave a Reply