እናት ፓርቲ በወላይታና አማራ ክልል አመራሮቹ እንደታሰሩበት ገለፀ

 እናት ፓርቲ በወላይታና አማራ ክልል አመራሮቹ እንደታሰሩበት ገለፀ

         እናት ፓርቲ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞንና በአማራ ክልል የሚገኙ አመራሮቹ  እንደታሰሩበት አስታወቀ።
ፓርቲው በአማራ ክልል እየተፈጸመ ነው ባለው አፈና፣ አቶ ሙሉጌታ የሺጥላ የተባለ የሰቆጣ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህርና የእናት ፓርቲ የሳይንት 2 ምርጫ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ፣እንዲሁም በህልውና ዘመቻው ወጣቱን በማስተባበር፣ በግንባር በመዋጋትና በማዋጋት ጭምር ከፍተኛ ዋጋ የከፈለና አሁንም በመምህርነት ስራ ላይ ተሰማርቶ ያለ አመራሩ፣ ከስራው ቦታ እንዳ “ታፍኖ” ከተወሰደ በኋላ ፓርቲው መግለጫውን እስካወጣበት ሃሙስ ድረስ ያለበት አለመታወቁን አመልክቷል።
ሌላኛው አቶ ታደለ ጋሾ የተባለ የአዊ ዞን ደጉሳ ሽኩደድ (ቲሊሊ) ከተማ የእናት ፓርቲ ም/ሰብሳቢ  በተመሳሳይ መልኩ “ታፍኖ” ከተወሰደ በኋላ እስካሁን አድራሻው አይታወቅም ያለው ፓርቲው፤ የእናት ፓርቲ ሞጣ ቅርንጫፍ፣ የፓርቲው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ ምግባሩ አስማረ ደግሞ፣በሞጣ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ እንደሚገኝ አመልክቷል።
የፓርቲው አባላት  በአማራ ክልል  ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክልል ወላይታ ዞንም መታሰራቸውን ያወሳው መግለጫው፤ በወላይታ ዞን የእናት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባልና የሶዶ አካባቢ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እጩ ተወዳዳሪ የነበሩት ወ/ሮ ስመኝ ታደመ መታሰራቸውንም አስታውቋል።
መንግስት በየአካባቢው በፓርቲው አመራርና አባላት ላይ የሚፈጸሙ  አፈናዎችና እስራቶችን እንዲያስቆም የጠየቀው እናት ፓርቲ፤ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የኢትዮጵያ  ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ድርጊቱን እንዲያወግዙና በመንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ  ጥሪ አቀርቧል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply