“እንደሀገር ወዴት እያመራን ይኾን?”

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ

(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና

የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

በሀገራችን በተለያዩ ወቅቶች የተከሰቱና እየተከሰቱ ያሉ ኹነቶች እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሳቸው ነባራዊ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ እንደሀገር የሩቁን እንኳ ትተን የቅርቡን ማስረጃ ብንመለከት CNN እንደዘገበው ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ተፈናቅለዋል፡፡

አብዛኛውን የሕዝባችንን ቁጥር የሚይዙት ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች እንደመኾኑ መጠን የዜጎች መፈናቀል ዋነኛ ተጠቂዎችም ከኹሉ በላይ እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ መፈናቀል ከኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሱ በላይ ማሕበራዊና ስነ ልቦናዊ ጫናው እጅግ ከፍተኛ ከመኾኑም ባሻገር የአኗኗር ዘይቤ ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖን ያሳድራል፡፡

ስለኾነም እንደሀገር በዚህ ፍጻሜ ውስጥ ትርጉም ባለውና በሌላ አካባቢ እንዳይደገም ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት ለምን አልተከናወነም? ስንል ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎችን እናገኛለን፡፡ እነዚህም፡-

1ኛ. ዜጎች ከመፈናቀላቸው በፊት – ይህ ሊከሰት እንደሚችል አይታወቅም ወይ? (በዋናነት በጸጥታ አካላትና በገዥዎች ዘንድ)

2ኛ. መፈናቀሎች ከማጋጠማቸው በፊት አስቀድሞ መከላከል – ለምን አልተቻለም?

3ኛ. የማፈናቀል ተግባራት ሲከናወን ስፋት ሳይኖረው በቀላሉ – ለምን መቆጣጠር አልተቻለም?

4ኛ. ያፈናቀሉ አካላት እነማን ናቸው? ለምን? ዓላማቸውስ ምንድነው?

5ኛ. ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ተለይተው ታውቀው – ለሌላው አስተማሪ የሚኾን ቅጣት ተጣለባቸው ወይ?

6ኛ. የተፈናቀሉ ዜጎችን በጊዜያዊነትና በዘላቂነት በኹለንተናዊ መንገድ ለመደገፍ ምን ኹለንተናዊ (ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ) ተግባራት ተከናወኑ?

7ኛ. ከቁሳዊ ድጋፍ ባሻገር ማሕበራዊ መስተጋብርና ስነ ልቦናዊ ቀውሶች ለመቀነስና ቢያንስ ወደ ነበረበት መልካም የአስተሳሰብና አመለካከት አድማስ ለመመለስ ምን ኹለንተናዊ ተግባራት ተከናወኑ? በማን? እንዴት?

8ኛ. ሕጋዊ ማዕቀፎች በተግባር ላይ ውለዋልን? የሕዝብ ውክልናን የያዙ ተቋማት በተቋማዊ አሰራራቸው መሠረት ምን ምን ተግባራትን አከናወኑ? ቀዳሚ አጀንዳቸውስ ማድረግ ቻሉ?

9ኛ. በሌላ አካባቢ እንዳይደገም የቅድመ መከላከል ኹለንተናዊ ተግባራት ተከናውነዋልን?

10ኛ. በሌላ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ድርጊቱን በተመሳሳይ ጊዜና ኹኔታ በአንድ ድምጽ ድርጊቱን በአደባባይ ትርጉም ያለው ተጽዕኖን በሚፈጥር መልኩ ማውገዝ ለምን አልቻሉም?

11ኛ. ምሁራን፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሚድያ በጋራ ለጋራ ጉዳይ ብለው በዚህ ዙሪያ ኹለንተናዊ ቅድመ የመከላከል፣ ድርጊቱ ሲፈጠር ድምጻቸውን የማሰማትና ድርጊቱ ከተፈጸመ በኃላ ደግሞ የማረጋጋትና ድጋፍ የማድረግ ኹለንተናዊ ተግባራትን በማከናወን ዙሪያ ምን እያደረጉ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ የተመለሱ አይመስሉም፡፡

ለአብነት እንኳ በዚህ ሳምንት እጅግ አሳዛኝ የኾነውን በኦሮሚያ – ሻሸመኔ ከተማ አንድ ወጣት እጅግ በሚያሳዝንና ልብን በሚሰብር በ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችል ቁልቁል ተዘቅዝቆ መሰቀል እና በአማራ ክልል ከተሞች በአደባባይ የተፈጸመውን ዘረፋና በኦሮምያ – በወለጋ የሰው ሕይወት በድንጋይ ተቀጥቅጦ በአደባባይ መጥፋት ስንመለከት እንድናነሣቸው የምንገደዳቸውን 7 ዐበይት ጥያቄዎች እናገኛለን፡፡

  1. ድርጊቱ በጥቂቶች አነሣሽነት በጥቂቶች የተፈጸመ መኾኑ የማያጠያይቅ ቢኾንም ብዙ ሕዝብ በአንጻሩ ድርጊቱ ሲፈጸም በአደባባይ ቆሞ ተመልክቷል፡፡ ብዙዎች ለምን ይህን መከላከል አቃታቸው? ተባባሪ ስለኾኑ ወይስ ፍርሃትና ስጋት እነሱም ዘንድ አለ? ጥቂቶች በአብዝሃዎች ላይ እንደምን ሊሠለጥኑ ቻሉ?
  2. የጸጥታና የህግ አስከባሪ አካላት የሕብረተሰቡን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታቸውንና ተልዕኳቸውን ለምን መወጣት አቃታቸው?
  • የመንግሥትና የፓርቲ መዋቅሮች ይህን ድርጊት አስቀድሞ ለመቆጣጠር ለምን አልቻሉም?
  1. የሃይማኖት ተቋማት የዘመናት አስተምህሮ – ሰውን እንደሰውነቱ የማክበርና የፈጣሪ ክቡር ፍጡር ስለመኾኑ የገለጹት ትምህርትና ተግባራዊ ፍጻሜ ሃይማኖተኛ በኾነ ሕዝብ – ከ97% በላይ የሚኾን ሕዝብ በዕምነት ውስጥ በሚኖርባት ሀገር እንዴት ሊፈጸም ቻለ? የሀገርና የሕዝብ ባሕል፣ ወግ፣ ልማድና ዕሴት ከወዴት ገባ? የሕዝብ ማሕበራዊ መስተጋብር እንደምን ይህን መታደግ አቃተው?
  2. ድርጊቱ በአደባባይ ይፈጸም ዘንድ ፈጻሚዎች ድፍረቱን ኬት አገኙ? እንዲህ ያለ ጭካኔ በአደባባይ ለመፈጸም እንደምን ለሰው ተቻለው? ማሕበረሰባዊ ያልተጻፈ ሕግና የተጻፈውን ህግ እንደምን ሳይፈሩ ቀሩ? ይህን በአደባባይ ሲፈጽሙ ህሊናና ሰብዓዊ ማንነት ከወዴት ገባ?
  3. ለዕውነት፣ ለፍትህ፣ ለሞራልና በፍቅር መኖር የሚሉ ዓለም አቀፋዊ የሰው ልጅ ዕሴቶች ከወዴት ገቡ?
  • በመላው የሀገራችን ከተሞች ደርጊቶቹ በሊቢያ ዜጎች በአሰቃቂና እጅግ ዘግናኝ በኾነ ኹኔታ መታረዳቸው ሲገለጽ ሕዝብ ያለማንም ቀስቃሽ በቁጣ፣ በቁጭትና በመራር ሃዘን በህብረትና በአንድነት በአደባባይ ወጥቶ ድርጊቱን እንዳወገዘው ኹሉ ያለ ልዩነት ማውገዝ ለምን አልተቻለም? እነዚህ ኹሉ ፍጻሜዎች ሲከናወኑ ብሔራዊ የሃዘን ቀናትን ማወጅ እንደምን ሳይቻል ቀረ?

ፈተና የነበረ፣ ያለና የሚኖር የማይቋረጥ ሂደት ነው፡፡ በኹለንተናዊ ፈተና ውስጥ መኖር ግድ እንደሚለንም ይታወቃል፡፡

እነዚህ በሁለት ክፍል የቀረቡ ጥያቄዎች “ሀገራችን ወዴት እያመራች ይኾን?” የሚል ጥያቄን እንድናነሣ ግድ የሚሉን ናቸው፡፡ “ዕውን እንደሀገር ወዴት እየሄድን ነው?” ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

Leave a Reply