‹‹እንደ ስልጢ ወረዳ እስካሁን ደሞዝ ያልተከፈለዉ የጤና ባለሙያ የለም›› የስልጢ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት

‹‹ባጋጠመን የበጀት ዕጥረት ምክንያት ያልከፈልነዉ የ5 ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ ብቻ እንጂ ደሞዝ በየወሩ እየከፈልን›› ነዉ ሲሉ የወረዳዉ ጤና ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ካሚል ጃቢር ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

የወረዳዉ የጤና ባለሙያዎች የሰሩበትን ደሞዝ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ በመጠየቃቸዉ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሰባቸዉ መሆኑን ለጣቢያችን መናገራቸዉን ከዚህ በፊት መዘገባችን የሚታወስ ነዉ፡፡

በወረዳዉ ጤና ጣቢያ የሚሰሩ ከ35 በመቶ በላይ የጤና ባለሙያዎችም ስራ ስለመልቀቃቸዉ እና ቀሪዎቹም የስራ መልቀቂያ ስለማስገባታቸዉም ሰምተን ነበር፡፡

‹‹በትርፍ ሰዓት ክፍያም ሆነ በደሞዝ ምክንያት ስራ የለቀቀ ማንም የለም ያሉት ሃላፊዉ ሌሎቹም በስራ ላይ ይገኛሉ›› ነዉ ያሉት፡፡

ቀሪ የ 5ወር የትፍር ሰዓት ክፍያዉንም የወረዳዉ መንግስት እከፍላለሁ እያለ ነዉ ያሉን አቶ ካሚል፤ለጤና ጣቢያዎች ግን አሁንም ድረስ በአግባቡ ደሞዝ እየገባ ነዉ ብለዉናል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ጊዜ ከወረዳዉ አስተዳደር ጋር በስፋት ተነጋግረናል ነገርግን ከእነሱ የምናገኘዉ ምላሽ ከመንግስት የሚላከዉ በጀት እየመጣ አይደለም የሚል ነዉ ብለዋል፡፡

ለወረዳዉ ከሚያስፈልገዉ 12 ሚሊየን ብር ዉስጥ በጀት ባለመኖሩ ምክንያት የሚላከዉ 8 ሚሊየን ብር ብቻ ነዉ የቀረዉን 4 ሚሊየን ብር በዉስጥ ገቢ ሸፍኑ የሚባል ነገር ነዉ ያለዉ ብለዉናል፡፡

በዚህ ምክንያት ነዉ የ 5 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ለመክፈል ያልቻልነዉ እንጂ ደሞዝ በየወሩ እየገባ ነዉ ብለዋል፡፡

የትርፍ ሰዓት ክፍያዉንም ቢሆን ከአራት ወራት ጀምሮ በአግባቡ መክፈል ጀምረናል ፤ አሁን ላይ የ 5ወራት የተጠራቀመ ዕዳ ብቻ ነዉ ያለብን ብለዋል፡፡

በወረዳዉ ካለፈዉ ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ የተጠራቀመ የ 6 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ያለፈዉ ወር ደሞዝ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተከፈላቸዉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጤና ጣቢያዉ ሰራተኛ ለጣቢያችን መናገራቸዉን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply