እንግሊዝ በኢትዮጵያ በችግር ዉስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች፡፡

ዛሬ በሲዉዘርላንድ ጄኔቫ የኢትዮጵያ መንግስት እና የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ማስተባበሪያ ቢሮ ለኢትዮጵያዊያን ተረጂዎች ዓለምዓቀፍ የሰብዓዊ ርዳታ ገንዘብ ለማሰባሰብ መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር ላይ ነዉ የእንግሊዝ መንግስት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ በኢትዮጵያ በችግር ዉስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገባዉ፡፡

ከእንግሊዝ መንግስት የሚለቀቀዉ ፈንድ በአየር ንብረት ለዉጥ፣ በግጭት፣ በበሽታ እንዲሁም በኢኮኖሚ ጫና ዉስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ የሚዉል ይሆናል ተብሏል፡፡

የአገሪቱ የዉጪ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ጸሃፊ በጥር ወር በኢትዮጵያ ተገኝተዉ በትግራይ ክልል ያለዉን ቀዉስ በአካል መመልከታቸዉን ቢሮዉ አስታዉቋል፡፡

የእንግሊዝ መንግስት በኢትዮጵያ በመቶሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የነፍስ አድን ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸ ሲሆን ፤ በተጨማሪም ከ4መቶ35 ሺህ በላይ የሚሆኑ በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት የሚሰቃዩ ህጻናት እና እናቶችን ጨምሮ ወደ 2መቶ30 ሺህ አፋጣኝ የህክምና አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸዉ ዜጎች ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ከ21 ሚሊዮን በላይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን የያዘችዉ አገራችን በዓለም ላይ ከፍተኛዉን ሰብዓዊ ቀዉስ እያስተናገደች መሆኑ ይገለጻል፡፡

ከ15 ሚሊየን በላይ ዜጎቿ የምግብ ደህንነት ስጋት ዉስጥ ያሉ ሲሆን፤ ከ4ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአገር ዉስጥ ተፈናቃይ ሆነዉባታል፡፡

ከፍተኛዉን ቁጥር የሚይዙት የትግራይ እና አማራ ክልሎች ሲሆኑ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ወደ 5 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ለከፋ ረሃብ የሚዳረጉ ይሆናል ተብሏል፡፡

የዛሬዉ የሰብዓዊ ርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በእንግሊዝ መንግስት፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ድጋፍ የተከናወነ ነዉ፡፡

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በዚህ ዓመት ለኢትዮጵያዊያን ተረጂዎች ድጋፍ ለማቅረብ 3.2 ቢሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ብሎ ነበር፡፡

በጄኔቫዉ መርሃ ግብር ከለጋሾች ለመሰብሰብ የታቀደዉ በጣም አስቸኳይ ለሆኑ ሰብዓዊ ድጋፎች የሚዉል 1 ቢሊየን ዶላር ነዉ፡፡

በእስከዳር ግርማ

ሚያዝያ 08 ቀን 2016 ዓ.ም

Facebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Source: Link to the Post

Leave a Reply